አዲስ አበባ፦ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ወጣቶች ታሪካቸውን እያወቁ የሚዝናኑበት ስፍራ ሆኗል ሲሉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምና የአብርሆት ቤተ መጽሐፍ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ ገለጹ።
ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሙዚየሙ በአንድነት ለሀገር ሉዓላዊነት የተከፈለውን መስዋዕትነት፣ የአርሶ አደሮችን ተሳትፎ፣ የሴቶችን ተጋድሎ የሚያሳይ ታሪካዊ ክፍል አለው። ይህንን ታሪካዊ ክፍል አውቆና ጎብኝቶ ከሙዚየሙ ለመውጣት አንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ አካባቢ ይፈጃል።
ይህም ጎብኚዎች ስለዓድዋ ድል ከብዙ በጥቂቱ እንዲያውቁ ያደርጋል ያሉት ኢንጅነር ውባየሁ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የዓድዋን ጦርነት ሁነቶች ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚሆኑ አዳራሾችን፣ ካፍቴሪያዎችን፣ ሲኒማ ቤቶችንና ሌሎች ለበርካታ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችን አካቶ የተሠራ ነው ብለዋል።
ሙዚየሙ ወጣቶች ታሪካቸውን እያወቁ የሚዝናኑበት ስፍራ ሆኗል ያሉት ኢንጅነር ውባየሁ፤ ከዚህ አኳያ ሙዚየሙ ለአሁኑ ወጣት መነሳሳት ብቻ ሳይሆን የሚፈጥረው የማሸነፍ እና ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ተምሳሌትንም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
ሙዚየሙ ለወጣቱ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያሳውቅ፣ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ እንዲያውቅ እና ጠንክሮ በመሥራት ሀገሩን ከፍ ማድረግ እንዲችል ያነሳሳል፤ ተምሳሌት ይሆናል ያሉት ኢንጅነር ውባየሁ፤ ሙዚየሙ ለጎብኚዎች ክፍት ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገራት መሪዎች እንደጎበኙት ተናግረዋል።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና መድረኮችም ተካሂደውበታል። ለዚህም ከሁለት ሺህ 500 በላይ እንግዶችን መያዝ የሚችል ፓን አፍሪካን አዳራሽ፣ 300 ሰዎች የሚይዝ የዓድዋ አዳራሽ፣ 160 ሰዎች የሚይዝ መካከለኛ አዳራሽ፣ 300 ሰው በአንድ የሚያስተናግዱ ሬስቶራንቶች፣ ሁለት ካፍቴሪያዎችና የሕፃናት ሙዚየም፣ የቴኒስ፣ የቅርጫት ኳስና ሌሎችን በውስጡ አካቶ የያዘ መሆኑ ሁኔታውን ምቹ አድርጎታል ብለዋል።
በሌላ በኩል በአንድ ጊዜ አንድ ሺህ ተሽከርካሪ መያዝ የሚችሉ ፓርኪንግ፣ ዘመናዊ ጂምና ሌሎችም አካቶ መያዙን ኢንጅነር ውባየሁ ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም