አዲስ አበባ፦ በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን ብቁ የትምህርት አመራር ማፍራት ወሳኝ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስቴር እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ትናንት ተፈራርመዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሀገሪቱ ልትደርስበት ካሰበችው ከፍታ መድረስ እንድትችል ብቁ የተቋም አመራር ያስፈልጋል። ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር የተደረገው አብሮ የመሥራት ስምምነት በተለይ በትምህርት ዘርፍ የበቁ አመራሮችን ለማፍራት ያስችላል።
መሪነት ራሱን የቻለና ከፍ ያለ ስብዕና የሚጠይቅ ኃላፊነት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ደግሞ ተከታታይ ስልጠና የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ በአመራር ደረጃ የሚሰጡ ስልጠናዎችን ለማሳለጥ እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ጠንካራ የተቋም አመራር ለመፍጠርና በተናጠል ለስልጠናዎች የሚወጡ አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስቀረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን ብቁ የትምህርት አመራር ማፍራት ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁ አመራር ያስፈልጋቸዋል፤ ከዚህ በኋላ በብቃት እንጂ በአካባቢ ተወላጅነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አይመሩም ብለዋል።
በቂ ችሎታ ያላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አመራሮች እንዲፈጠሩ በእቅድ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ የትምህርት ሚኒስቴር በሀገሪቱ የትምህርት ልማት ላይ እያካሄደ ያለውን ሪፎርም መደገፍ ይፈልጋል። ሪፎርሙ ስኬታማ የሚሆነው ብቃት ባለው አመራር ሲመራ ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ዘርፍ ጠንካራ የተቋም አመራር ከማፍራት አኳያ ውስንነት አለ ብለዋል።
ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነት የሚታይ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ የአመራር ልማት ሥራ እስከአሁን በበቂ ደረጃ አለመሠራቱን ገልጸዋል።
መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ሳይንሳዊ አካሄድ መከተል እንደሚገባ በመግለጽ፤ አመራሮች የሚመሩትን ተቋም በሃሳብ ልቀው መምራት እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
ዓለም ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንፃር አይተው መምራት እንዲችሉ የአመራሮቹን አቅም በትምህርትና ስልጠና ማብቃት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ አካዳሚው፤ ነገ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ጠንካራ ተቋማት መፍጠር ካስፈለገ አመራር ላይ መሥራት የውዴታ ግዴታ ነው ብለዋል።
በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮችን አቅም ለመገንባት ስምምነቱ ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተው፤ የመግባቢያ ስምምነቱን በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሽኔ እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የአመራር ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሠረት ደስታ ተፈራርመዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም