አዲስ አበባ፡– በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የልማት ሥራዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ከተማ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ከዓመት በፊት የአማራ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ነበር፡፡ የክልሉን ሰላም ለመመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የፌዴራል ፀጥታና ደህንነት እንዲሁም የክልሉ የፀጥታ ተቋማት ባደረጉት ርብርብ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላምም ክልሉ ላይ የልማት ሥራዎች በአግባቡ እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በጎንደር ተገኝተው የፋሲል ግንብን እድሳት፣ የመገጭ ግድብን ግንባታ እንዲሁም በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት መጎብኘታቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የግድቡ ግንባታ ከመስኖ ልማት ባለፈ ለጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ በመሆኑም ግንባታው ሌት ከቀን በከፍተኛ ፍጥነት በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፋሲል ግንብም ከጎንደር አልፎ የሀገሪቱ ሀብት የሆነ ትልቅ ታሪካዊ ቅርስ መሆኑን ገልጸው፤ ጥንታዊነቱን ጠብቆና ፈርሰው የነበሩ ጥንታዊ ግንባታዎችን አካቶ በከፍተኛ ጥራት በመታደስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም ከተማዋን ጥንት ወደነበረችበት ከፍታ እየመለሳት እንደሆነ ተመልክተናል ብለዋል፡፡
ከፕሮጀክቶች በተጨማሪ ክልሉ ላይ የግብርና ሥራዎች በአግባቡ እየተከናወኑ እንደሆነ መመልከታቸውንም ገልጸዋል፡፡መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ነገሮችን አፍርሶ አዲስ ነገር መገንባት ላይ የሚያተኩር ታሪክ ነበረን ያሉት አቶ ተመስገን፤ ብልጽግና የሚከተለው አካሄድ ግን ነገሮችን እያስቀጠልን መሻሻልና መጨመር ያለበትን ጉዳይ ደግሞ እየጨመርን መሄድ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ሪፎርሙ ያልገባቸው አንዳንድ አካላት በኃይልና በጠመንጃ አፈሙዝ ለውጥ አመጣለሁ ብለው ክልሉን ችግር ውስጥ ከተውት እንደነበር አመልክተው፤ መጀመሪያ ላይ ኅብረተሰቡንም አደናግረውት ነበር፡፡ አሁን ግን ነቅቶ ሰላሙን እያስከበረ ይገኛል ብለዋል፡፡
በፀጥታ ችግር ከታመሱ ከተሞች አንዷ ጎንደር እንደነበረች አስታውሰው፤ አሁን አንጻራዊ ሰላም ያለበት ነው፡፡ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ነው፡፡ ይህ ሥራ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር የተሳሳተ እሳቤ ያላቸው አካላት ከድርጊታቸው እየተቆጠቡ ይመጣሉ፡፡ ሰላምን መርጠው ለሚመጡም መንግሥት ምንጊዜም ለሰላም በሩ ክፍት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የአማራ ክልል አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም ተስፋ ሰጪና ከችግሩ እየተሻገረ ነው፡፡ችግር ውስጥም ሆኖ ልማቱን እያረጋገጠ እንደሆነ የሚያመላክት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
የክልሉ ሰላም በዚህ ደረጃ እንዲገኝ ሕዝቡ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፀጥታና ደህንነት ተቋማት እንዲሁም የክልሉ የፀጥታ ተቋማት ላደረጉት ርብርብ ምስጋና አቅርበው፤ ከሰላም አፈንግጠው የሚገኙ ጥቂት አካላት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር እና አካባቢው ካደረጉት ጉብኝት በተጨማሪ በሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና ሥራዎችን መጎብኘታቸው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም