ዲጂታል መታወቂያ – ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ

በሁሉም መስክ ዲጂታል ኢትዮጵያን እንደ እ.ኤ.አ በ2025 እውን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ የፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ይጠቀሳል። የዲጂታል ስትራቴጂ 2025 ዕቅዱ አካል የሆነው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የተጀመረው ብዙ ነገሮችን ታሳቢ አድርጎ ነው። የሁሉንም ነዋሪ ረቂቅ የባዮ-ሜትሪክና ዲሞግራፊክ መረጃን በመውሰድ፤ ይሄንኑ ወደ ልዩ መለያ መቀየርና በልዩነት የመታወቅ ሥርዓትን ማረጋገጥ በዋናነት ይጠቀሳል።

ዛሬ ብዙ ሀሰተኛ መረጃዎች ወይም እየተመሳሰሉ የሚሠሩ ወንጀሎች በበዙበት ዓለም ማነው በልዩነት መታወቅን የማይፈልግ? በኢትዮጵያም እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል ሊለይ የሚችል ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አንፃር ገና የሚቀር ነገር በመኖሩ ያልተማረረና የችግሩ ሰለባ ያልሆነ ዜጋ የለም። ተመሳስለው የሚከፈቱ እንደ ፌስ ቡክ፣ ቴሌግራምና ሌሎች የማህበራዊ ድረ ገጽ አገልግሎቶች፣ የሀሰት መታወቂያ፣ ወደ ንግዱ ዓለም ስንገባም ደግሞ ገበያ ለመሳብ ሲባል ታዋቂነትና ገበያ ያለውን ድርጅት የንግድ ስያሜ ምርት ላይ መለጠፍና ማታለል ልዩ መለያ ስለሌለን የሚገጥሙን ችግሮች ናቸው።

እውነት እንደዚህ ዓይነቶቹን ወንጀሎች በልዩነት በመታወቅ ሊያሸንፋቸው የማይፈልግ ማን አለ? በልዩነት መታወቅ የማይፈልግና በልዩነቱ በመታወቁ ሊያገኛቸው የሚገቡ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉ የማይገነዘብ ዜጋ አለ ብዬ አላምንም። አንዳንድ ሰዎች ብሄራዊ መታወቂያ በማውጣት በልዩነት መታወቁ የሚያስገኘው ጥቅም ስለገባቸው ይመስላል በተለይ ዲጂታል አይዲ (መታወቂያ) የተጀመረ ሰሞን ወደ ምዝገባ ቦታዎች ሲተሙ ተስተውሏል። የመመዝገቢያ ቦታዎችም በብርቱ ተጨናንቀው ሰንብተዋል።

ብሄራዊ መታወቂያ እንደግለሰብ፤ እንደ አጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ዜግነት፤ እንዲሁም እንደ ተቋምና እንደ ሀገር የሚሰጠውን ጥቅም ሁላችንም ልንረዳ ይገባል። ዓለምን አንድ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆናችን መዘመናችንን የሚያሳይ፤ ከፍታችንን የሚያጎላ በመሆኑ እያንዳንዳችን ኩራት ሊሰማንም ይገባል። ያልተመዘገብንም በፍጥነት ለመመዝገብ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። በቅርቡ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለመመዝገብ ላቀረበው ጥሪ መልስ መስጠት ይኖርብናል፤

ብሄራዊ መታወቂያ እንደ ቀበሌ መታወቂያ አካባቢን ብቻ የሚገልጽ ሳይሆን ሀገርን ተሻግሮ ማገልገል የሚችል ነው። ዓለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለችበት በዚህ የቴክሎጂ ዘመን ብሄራዊ መታወቂያ አለመያዝ ራስን ከዓለም ማህበረሰብ እና መታወቂያውን በመያዝ ከሚገኙ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንደ ማግለል ነው። ወደፊት ብሄራዊ መታወቂያ መያዝ ግዴታ የሚሆንበት አሠራር እንደሚኖር መገመት አይከብድም፤ እየዘመነ ከሚሄደው ዓለም ጋር ራስን አስተሳስሮ መጓዝ ያስፈልጋል።

ቀድመው የነቁ ጥቂት ሰዎች ብሄራዊ መታወቂያቸውን በእጃቸው አስገብተዋል፤ አንዳንዶችም በሂደት ላይ ናቸው፤ አንዳንዶች ግን ቸልተኛ ሆነዋል። ይሄ ቸልተኝነት የሆነ ቀን ዋጋ የሚያስከፍል እንደሚሆን መርሳት አያስፈልግም ፤ ምክንያቱም መታወቂያው ለብዙ ጉዳዮች ተቀባይና ተፈላጊ የመሆኑ ነገር ስለማያጠራጥር ። ይህንን የተረዱ አንዳንድ ተቋማትም ሠራተኞቻቸው የዚህ መታወቂያ ባለቤት እንዲሆኑ ከወዲሁ እየሠሩ ይገኛሉ።

ለአብነት አንጋፋውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መመልከት እንችላለን። በእርግጥ የዚህ ተቋም ዘመናዊነትን መከተል ከሚሰጠው የላቀና የረቀቀ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አንፃር ላይደንቀን ይችላል። እንደውም ቀድሞ ወደ ሲስተሙ አለመግባቱ ወይም መዘግየቱ ትዝብት ላይ ይጥለዋል። ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ሥርዓቶችን አስተሳስሯል።

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለሀገር ውስጥ በረራዎች በጉዞ ሰነድነት መጠቀም ወደሚያስችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። አየር መንገዱ በፋይዳ የመንገደኞች አገልግሎት፤ ምዝገባ ከማስያዝ (Booking) ጀምሮ እስከ መሳፈር ድረስ ያሉትን ባዮ ሜትሪክ መረጃን በመጠቀም የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማቀላጠፍ እና የተሻለ ለማድረግ አቅዷል።

ዲጂታል መታወቂያው ዜጋን እንደ ዜጋ ሀገርን እንደ ሀገር ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃና የከፍታ ማማ ላይ የሚያወጣ፤ የግለሰቦችን ማንነት ማወቅ ለሚፈልግ አካል በሙሉ ከወረቀት ባሻገር አስፈላጊውን መረጃ የሚሰጥ፤ ዓለም በተሳሰረችበት ኔትወርክ ውስጥ የሚያስገባና ከሚገኘው ሀገር አቀፍም ይሁን ዓለም አቀፍ በረከት ሁሉ ለመቋደስ የሚያስችል ነው።

ወደፊት የሀገሪቱ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝቦች ማንነታቸውን በሚገልጽ አንድ ሲስተም ውስጥ መካተታቸው የማይቀር ነው። በፌስ ቡክ ላይ የሰዎችን ስም ጽፈን እንደምናገኝ ሁሉ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ ሲበለጽግ ስለማንኛውም ሰው ማንነት በቀላሉ መረዳት የምንችልበት አሠራር መፈጠሩ የሚቀር አይመስልም። ይህ ደግሞ የግለሰቦችን ፣ የተቋማትን እና የሀገራትን አሠራር ለማቀላጠፍ በእጅጉ የሚጠቅም ነው።

በተቋም ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም እያንዳንዱ ዜጋ ብሄራዊ መታወቂያውን አውጥቶ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፤ መታወቂያው ከሚኖረው ፋይዳ አንጻርም ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ግድ ይለዋል። እያንዳንዱ ዜጋ በልዩነት መታወቅ እንደሚሻ ሰው፤ እንደ ዜጋም አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ መታወቂያውን በእጁ ሊይዝ ይገባል።

እስካሁን ተመዝግቦ መታወቂያውን የያዘው ዜጋ ቁጥር አገልግሎቱ በተጀመረበት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚኖረው ነዋሪ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ትንሽ ነው። መታወቂያው በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት መገንዘብ ይችላሉ ተብለው ከሚታሰቡትና በየተቋሙ ከሚሠሩት የመንግሥት ሠራተኞች መካከል እንኳን መመዝገብ የቻሉት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። መታወቂያውን ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማትም ይሁኑ ሌሎች አመራሮቻቸውን እና ሠራተኞቻቸውን በማስመዝገብ መታወቂያውን በመውሰዱ ረገድ አርአያ ሊሆኑ ይገባል።

አሁን ላይ የዚህን የብሄራዊ መታወቂያ ፈላጊና ተመዝጋቢ ቁጥር ለማሳደግ የምዝገባ ቦታዎችም እየሰፉ መጥተዋል። የብሄራዊ መታወቂያ ምዝገባ በሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ሁለት ቅርንጫፎች እየተካሄደ ነው። ከዚህም አልፎ ታች በመውረድ በ11ዱም የክፍለ ከተማና በ119ኙም የኤጄንሲው የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች የምዝገባ አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው።

በቅርቡም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ በ16 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እያካሄደ መገኘቱን ገልጾ፤ ዜጎች እንዲመዘገቡ ጥሪ ሲያቀርብ ተደምጧል።ይሄን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ ነገ በዚህ ተቋም ያለ ብሄራዊ መታወቂያ በቀበሌ መታወቂያ ብቻ አገልግሎት አገኛለሁ ብሎ ማሰብ የለበትም።

ዘመኑ የሚፈልገው ስለ አንድ ግለሰብ ሁሉንም መረጃ አካቶ የያዘና በአንድ ቋት ውስጥ ተደራጅቶ የተቀመጠ ብሄራዊ መታወቂያ ስለሆነ የቀበሌ መታወቂያዎችን ቀስ በቀስ ከአገልግሎት ውጪ እያደረጋቸው የሚሄድ መሆኑን መረዳት አይከብድም። ይህን አሠራር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው ዓለም የሚከተለው መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል። ከዓለም አሠራር ጋር የሚጣጣም ሥርዓትን መከተልም መሠልጠን ነው።

ዲጂታል መታወቂያ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ፤ ማህበራዊ ደህንነትን የሚያረጋግጥ፤ የግለሰቦችን ውጣ ውረድ የሚቀንስ፤ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚያመጣ፤ ተቋማትን በበይነ መረብ የሚያስተሳስር፤ የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ከአንድ መስኮት አገልግሎት ወደ ቨርችዋል አገልግሎት የሚያሸጋግር ነው።

እንፍጠን! በእጃችን ያሉትን ከ45 ሚሊዮን በላይ ዘመናዊ የእጅ ስልኮች ለብሄራዊ መታወቂያው ምዝገባ ሂደት እናውላቸው። ዛሬውኑ ጊዜ ሳናጠፋ ብሄራዊ መታወቂያችንን በእጃችን እንያዝ። እግረ መንገዳችንን ወንጀልን እንከላከል! በጋራም ከሌሎች ዓለማት ጋር በመዘመን እድገታችንን እናፋጥን!!!

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You