ላለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፍጆታ በመሆን በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የውሀ ፖለቲካ ነው ብል ተሳሳትክ አትሉኝም። በርካታ የታሪክ ምሁራንም ይሄን እውነት በመደገፍ የተለያዩ ሀሳቦችን ሲያነሱ ቆይተዋል። አንዳንዶች እውነቱን ሲቀበሉ የተቀሩት ደግሞ በራስ ወዳድነት የበላይነታቸውን ሊያሳዩ ሲሞክሩ ታዝበናቸዋል። በቀይ ባሕርና በዓባይ ውሀ ላይ የሚነሳው ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የይገባኛል ንትርክ ከትናንት ወደዛሬ የመጣ ወቅታዊ የፖለቲካ አጀንዳ በመሆን ብዙዎች በአንክሮ እየተከታተሉት ይገኛሉ።
ይሄን ጉዳይ በአንክሮ ከሚከታተሉ ሀገራት መሀል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ስትሆን ዓለም አቀፉን ስምምነት በተከተለ የአብሮ መስራት አቋም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ፍቃደኝነቷን በመግለጽ ላይ ትገኛለች። ቀይ ባሕርም ሆነ ዓባይ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ይዞታ እንደሆኑ በታሪክ አጥኚዎች የተረጋገጠ ቢሆንም እውነታውን የካዱ ሀገራት ግን ራስን ብቻ ለመጥቀም በተነሳሳ ፍላጎት የአብሮ እንስራ ጥያቄን አሻፈረኝ ብለዋል።
ቀይ ባሕር እና ዓባይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ታሪካዊ ተዛምዶ በተመለከተ መጽሀፍ በመጻፍና ጥናት በማድረግ እውነታውን ከሚናገሩት መሀል የታሪክ ምሁሩ አቶ ዳኛው ተስፋው አንዱ ናቸው። ቀይ ባሕር በጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ላይ ሰፊ ድርሻ ያለው፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በመምራት በዓለም ላይ ካሉ በጣት ከሚቆጠሩ ስልጡን ሀገራት መሀል ወሳኝ በመሆን የሚጠራ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ባለው ሁኔታ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዚህ ጋር አያይዘው ኢትዮጵያ ካላት የኢኮኖሚ ግዝፈትና በቀጣናው ካላት ተጽዕኖ ፈጣሪነት አኳያ የባሕር በር እንደወደብ ሳይሆን እንደሕልውና የሚታይ ጉዳይ ነው ሲሉ ወሳኝ እውነታን ገልፀዋል። አሁን ላይ ነገሮች ቀልድና ዋጋ የሌላቸው ሊመስሉ ይችላሉ። ጥቅማቸው ምን ያክል እንደሆነ ነገ ላይ ነው የሚታወቀው። የባሕር በር ለሚመጣው ሀገራዊ እቅድና ትልም ከዛሬ ይልቅ ለነገ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ይሄ የታሪክ ምሁሩ ንግግር በቀይ ባሕርና በዓባይ ላይ የጀመርነው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በፍላጎትና በይገባናል የሚያበቃ ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ የሚጠቁም ነው። ሰፊና ግዙፍ በሆነ ሀገርና ሕዝብ መሀል በእርግጥም ሚዛን ደፊ እውነታ ነው። የታሪክ ምሁሩ ሰፊ የጥናት ዳሰሳ እንደሚያሳየው ከሆነ ሀገር እየሰፋ፣ ሕዝብ እየበዛ ነው የሚሄደው።
በዚህ ስፋትና ብዛት መሀል ደግሞ የፍላጎት ጥያቄ ይመጣል። ፍላጎትን ለማሟላት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በኢምፖርትና ኤክስፖርት በበቂ ሁኔታ መሳለጥ ያስፈልገዋል። የኢኮኖሚው ሁኔታ እንዲቀላጠፍ ራስ ገዝ የሆነ የወደብ አስፈላጊነት ወሳኝ ሆኖ ይመጣል። ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ወደብ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይም ጭምር ነው ስንል ለዚህ ነው።
በአሁኑ ሰዓት የዓለም ትኩረት ውሀ ላይ ነው። እነ ነዳጅ ወርቅና ውድ ማዕድናት የውሀን ያክል ዋጋ የማያወጡበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ይሄ ዘመን ‹የውሀ ገንቦ› በሚል በቁልምጫ ለምትጠራው ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው። በአንድ ዓላማ ያሉንን የውሀ ሀብቶ ቻችንን በተገቢው መንገድ ለተገቢው ዓላማ መጠቀም ከቻልን በኢኮኖሚው ሆነ በፖለቲካው የበላይነትን ከማምጣት ባለፈ የደህንነት ዋስትናም እናገኛለን። ይሄ ሳይሆን ቀርቶ በያዝ ለቀቅ ወይም ደግሞ ደጋፊና ተቺ በመሆን ጎራ የምንለይ ከሆነ በረከቶቻችን ጣጣ ይዘውብን የማይመጡበት ምንም ምክንያት የለም።
ላነሳነው ጥያቄና ወደፊትም ለምናነሳው ህዝባዊ ጥያቄ የጋራ አቋም መያዝ እንዲህ ባለው ጉዳይ ላይ ወሳኝነት አለው። ሕዝባዊ አንድነት ያለውን ፋይዳ በተለያየ አጋጣሚ እናስተውላለን። በሀገር ደረጃ የተመዘገቡ ደማቅ ድሎች በአንድ ዓላማ ለአንድ የቆምንባቸው ናቸው። በዓባይ ግድብ ላይ እያሳየነው ያለው የበላይነት የአብሮ መጽናት ሕዝባዊ ዓላማ እንደሆነ ግልጽ ነው። በቀይ ባሕር ላይ የነበረንን ይዞታ በአዲሱ ትውልድ የይገባኛል ጥያቄ መልሰን ወደነበርንበት የከፍታ ዘመን መመለስ የጋራ የቤት ስራችን ነው።
ሀያላኑን ጨምሮ ብዙ ሀገራት በውሀ ፖለቲካ ላይ አነጣጥረዋል። በአሁኑ ሰዓት ዓለም ከተሳሰረችበትና ወደ አንድ አቋም ከመጣችበት ጉዳይ አንዱ የውሀ ፖለቲካ ነው። ቀይ ባሕር፣ ስዊዝ ካናል፣ ኤደን ባህረ ሰላጤ የንግድ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ የሌላም ሌላ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ኮሪደር ናቸው። ብዙዎች በበላይነት ሊቀራመቱት በእኔ እበልጥ እኔ ሽኩቻ ውስጥ ከገቡ ሰንበትበት ብለዋል።
እዛ አካባቢ የሚሆን የትኛውም ድርጊት ዓለም አቀፍ ትኩረትን ለማግኘት ደቂቃ አይፈጅበትም። ቦታው አህጉራት ከአህጉራት፣ አውሮፓ ከአፍሪካ እና ከኢሲያ ጋር ሌሎችም እንደዚሁ አንዱ ከአንዱ ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ስለሆነ ትኩሳቱ የጋራ ነው። ለአብነት ብንጠቅስ በ1960 ገደማ በእስራኤልና በአረቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት ብዙሀኑን የነካ የኢኮኖሚ ቀውስ ተፈጥሮ ነበር።
እንደታሪክ አዋቂው ዳኛው ተስፋው ገለጻ፤ ዓባይ አልፎ ከሚሄድባቸው ሀገራት ተጨማሪ ለመዳረሻነት የሚፈልጉት ብዙ ሀገሮች እንዳሉ ሰምተናል። ሳውዲ አረቢያ በግብጽ በኩል ተንጠራርታ መዳረሻዋ ልታደርገው ሙከራ እንዳደረገች፣ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት እንደዚሁ መዳረሻቸው ሊያደርጉት ብርቱ ፍላጎት አላቸው።
ግብጽ በተሳሳተ ስምምነት በዓባይ ውሀ ላይ ፈላጭ ቆራጭ በመሆን ብዙ ዘመናትን ተጉዛለች። ለቀረቧት ወዳጅ ሀገራት እንደእርጎ እንኳን ደህና መጣችሁ ስትል ከውሀዋ ቀድታ መስጠት ልማዷ ነው። በታሪክ የሚታወሰው ከእስራኤል ጋር በነበራት ጉርብትና በመሪዋ በኩል ‹ዓባይን ውሀ አብረን እንጠጣለን› ስትል የተናገረችው ነው። ይሄ የድፍረት ንግግሯ በዓባይ ላይ ያላትን የበላይነት በመሻር ዓባይ ወደትውልድ ሀገሩ በመመለስ ጥመኞችን ሊያረሰርስ ግድብ ሆኖ መጥቷል።
እንደኢትዮጵያ ያሉ አንድና ሁለት በአብሮ መስራት መርህ የሚያምኑ ሀገራት ቢኖሩ ዓባይና ቀይ ባሕር ይሄን ያክል መከራከሪያ ባልሆኑ ነበር። የዓባይ ውሀ ካየነው ብዙ ነገሩ ከኢትዮጵያ ነው፣ ቀይ ባሕርም በቅርብ ርቀት ላይ ያለ ከታሪክ የተዋረሰ ግዛቷ ነው። እንደዛም ሆኖ ለብቻዬ ልጠቀም የሚል የላትም። ለየት የሚያደርገውና እኛንና ጉረቤት ሀገራችንን ስለፍትህ ላይና ታች ያስቀመጠው 12 የሚሆኑ ወንዞቻችን ድንበር ተሻጋሪ ሆነው ሌሎች የመኖር ዋስትና መሆናቸው ነው።
እነዚህ ሀገራት ዓባይ ብለን ግብጽ እንደምንለው በእኛ የተፈጥሮ ጸጋ ያተረፉ፣ የከበሩ ሀገራት ናቸው። የሚገርመው ደግሞ ውሀችንን ጠጥተው ያደጉና በውሃችን ሀገር የሆኑ ሀገራት ዛሬ ላይ ስለቀይ ባሕር ጥያቄ ስናነሳ መከፋታቸው ነው። አስራ ሁለት ወንዞቻችን ድንበር አልፈው ወደጎረቤት ሀገራት ሲሄዱ እኛ ከሌሎች ያገኘነው ምንም አልነበረም። በተቃራኒው ግብጽ ዓባይን በተሳሳተ ትርክት የራሴ ነው ብላ እንዳመነችው እነዚህም ሀገራት ስለወንዞቻችን ምስጋናን ከመቸር ይልቅ ስለወንዞቻችን ጥርጣሬን ነው ያስቀደሙት። ወደብ ያስፈልገናል፣ ዓባይን ገድበን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት መውጣት እንፈልጋለን ስንል እንኳን ይሁንታን አላሳዩም።
ባለን ታሪካዊና ወቅታዊ ግዝፈት የቀይ ባሕርም ሆነ የዓባይ ጉዳይ በዋናነት እኛን የሚታከክ ነው። ችግሩም መፍትሄውም ምስራቅ አፍሪካን በተለይም እኛን ነክቶ የሚያልፍ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ሀገራት ጋር ባለን ንጽጽር ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነን የመታየት እድላችን የገዘፈ ነው። በሕዝብ ቁጥር፣ በኢኮኖሚ ግስጋሴ፣ በቀጣናው ባለን ተደማጭነት በውሀው ፖለቲካ ላይ ፊተኝነትን እንድናገኝ አድር ጎናል። የታሪክ ተመራማሪው ይሄን ጉዳይ ሲገልጹ ‹ባላት ወቅታዊ ቁመና ኢትዮጵያ በዓባይና በቀይ ባሕር ላይ እንደተጽዕኖ ፈጣሪና እንደስጋት የምትታይ ናት› ብለው ነው።
የዚህ ዘመን ‹ሰማያዊ ወርቅ› በሚል ስም የሚጠራው ውሀ ባላቂ የተፈጥሮ ሀብት ስር ብዙዎች አትኩሮት የሚያደርጉበት ከሆነ ሰነባብቷል። ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት በመሆን የሚነሳው ደግሞ ተተኪ አለመሆኑ፣ ለመገኘት ብዙ መስዋዕት የሚጠይቅ መሆኑ፣ ለሕይወት እጅግ ወሳኝ መሆኑ እና ውሱን የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ ነው። ውሀ ያለው ሀገር ነዳጅ ካለው ሀገር በበለጠ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቁመና ላይ ለመገኘት ቅርብ እንደሆነ የመስኩ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ።
በወቅቱ የነበሩ ወሳኝ ጉዳዮች ለአንደኛውና ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መከሰት ምክንያት ሆነዋል። እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት በውሀ እንደሚነሳ የሚተነብዩ የታሪክ ሰዎች እየተፈጠሩ ነው። ጦርነት በውሀ ይነሳል ብሎ የገመተ ማን ነበር? ከምድራችን 71 በመቶ ውሀ እንደሆነ ከዚህ ውስጥ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነው 3.5 መሆኑ ጉዳዩን ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል። እንግዲህ ዓለም ግብግብ የያዘው 5 ፐርሰንት ባልሞላ በዚህ ውስን የውሀ ድርሻ ላይ ነው።
እንደሀገር ተፈጥሮ በብዙ የባረከችን ሕዝቦች ነን። በተለይ ውስን በሆነው የውሀ ሀብት ላይ በርካታ ጸጋዎች ተችሮናል። ከጸጋዎቻችን መሀል ደግሞ አባይና ቀይ ባሕር ይገኙበታል። የታሪክ ምሁሩ ዳኛው ተስፋው ‹ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር እና የዓባይ ባለይዞታ ናት› ሲሉ ጠበቅ ያለ መልእክታቸውን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አስፍረዋል። ከዚህ የባለታሪክ ሀሳብ ተነስተን እያደረግነው ያለው የሕዳሴ ግድብም ሆነ የወደብ ጥያቄ ሕጋዊና በራስ ተፈጥሮ ላይ እንደመጠቀም የሚቆጠር መሆኑን እንረዳለን።
አሁን ባለው የውሀ ፖለቲካ ቀይ ባሕርም ሆነ ዓባይ ከፍታዊ ተጠቃሚነት ባለፈ እንደህልውና ሊታዩ የሚችሉ ናቸው ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ያሳስባሉ። ማስተንፈሻ ኮሪደር እንፈልጋለን ስንል ለአሁናዊ ጉዳይ ሳይሆን ከቀጣዩ የሕዝብ ቁጥርና የትውልድ ፍላጎት አንጻር አብሮ ሊታይ የሚገባው ነው ይላሉ። የወደብ ጉዳይ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጎን ለጎን የሉአላዊነት እና የደህንነት ጉዳይም ጭምር ነው። የታሪክ ተመራማሪው ዳኛው አስፋው ይሄን እውነታ ‹ቀይ ባሕርን በሸሸነው ቁጥር የሀገራችን ሕልውና እየተቃወሰ ይሄዳል› ሲሉ ነው የገለጹት። ይሄ እውነታ እንደ መልዕክት ለሁላችንም አንቂ ደወል ሆኖ የሚቀመጥ የቤት ስራችን ነው።
በንግድ ልውውጥ ሂደት ወቅት ርካሽ በመሆን ተመራጩ የባሕር ላይ ማጓጓዣ ነው። ለሸቀጦች፣ ለምርቶች፣ ለጥሬ ሀብቶች ለሌሎችም የኢምፖርትና የኤክስፖርት ንግድ የባሕር ትራንስፖርት ወሳኝ በመሆን ጥቅም ላይ ይውላል። ለዚህ እንደጥሩ የሚነሳው ቀይ ባሕር ነው። በኢሲያ፣ በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል በመኖሩ እንደማዕከል በመሆን ከብዙዎች ለብዙዎች ግልጋሎት በመስጠት ቀዳሚ ነው።
የኢትዮጵያ ነባር አቋም ሕብረት ፈጥረን በጋራ እንልማ የሚል ነው። ሰጥቶ የመቀበል መርህ በጋራ ተጠቃሚነት የሚያምን የጋርዮሽ መስተጋብርን የሚያጎለብት ነው። ቀይ ባሕር ካለው ግዝፈትና እየሰጠ ካለው ብዙ ጥቅም በአብሮ መስራት ካልሆነ በብቻ ፍላጎት የሚሆን አይደለም። ሶማሊያ በዋቢ ሸበሌና በገናሌ ወንዞቻችን ሕልውናዋን ስታቆም ለምን አላልንም። ግብጽና ሱዳን በዓባይ ውሀ ስልጣኔን ሲያቆሙ ደስ አለን እንጂ አልተቃወምንም። ተራችን ደርሶ በሀብታችን ለመጠቀም ስንሞክር መተባበር እንጂ መቃወም ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። እንዲህ ያሉ የብቻ ፍላጎቶች ኢትዮጵያን ሳይሆን ራሳቸውን የሚጎዳ እንደሆነም የታሪክ አጥኚዎች ይገልጻሉ። ስለዚህ ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለኛ በሚል በመተባበር መንፈስ ሀብታችንን ማልማትና በጋራ መጠቀም ይኖርብናል የሚለው የዛሬው መልዕክቴ ነው። አበቃሁ!
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም