ዓለም በርካታ ቴክኖሎጂዎችን አስተዋውቃናለች። ሰዎች የሚገለገሉባቸው፣ ሕይወታቸውን የሚያቀሉባቸው ፣ አጃኢብ የሚያሰኟቸው ቴክኖሎ ጂዎች በቅርበት ማየት ችለናል። ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነውን የእጅ ተንቀሳቃሽ ስልክ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ሰዎች ቀደም ባሉት ዘመናት አጠገባቸው የሌለን አርቆ የሚገኝ ወዳጅ ዘመዳቸውን የሚያገኙትና ናፍቆታቸውን የሚወጡት አንድም በስልክ ድምፃቸውን በመስማት ካልሆነም ደብዳቤ በመጻፍ እና በፖስታ ቤት እንዲደርስ በማድረግ ነበር። ይሄም ምን ያህል ጊዜን እንደሚወስድና ሰፊውን የሰዎችን ሀሳብ በቁንጽል መልዕክት ብቻ የሚተላለፍበት እንደነበር አንዘነጋውም።” በስልክ አነጋግሪኝ በቀጭኑ ሽቦ ትዝታ እንዲመጣ ደርቦ ደራርቦ… ” ተብሎም ተዜሞለታል የቤት ስልክ።
አሁን ላይ ደግሞ ዘመኑ ባፈራቸው ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች በድምፅ ብቻ ሳይሆን በምስል ተደግፎ እየተያዩ ሀሳብን ከነስሜቱ መግለጽ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሀሳብን በተለያየ መንገድ በአጫጭር የጽሁፍና የድምጽ መልዕክት በቀላሉ ማስተላለፍ ተችሏል። በተለያየ የገበያ ስፍራ ላይ ሳይገኙ ግብይትን መፈጸም እንዲሁ ዛሬ ቀላል የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እንኳንስ በሀገር ውስጥ ከውጪ ሀገር ጭምር ከወዳጅ ዘመድ የተላከ ስጦታ ሳይቀር አለንበት እቤታችን ድረስ የሚመጣበት ዓለም ወደ አንድ ኳስነት እየተቀየረች ያለችበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ብዙ የሚታዩ ከጊዜው ጋር አብረው የዘመኑ ነገሮች ሕይወትን ቀለል እያደረጉ ይገኛሉ። ከሀገር ውጪ በገበያ ላይ በአይን ያዩትንና የተመኙትን የራስ ማድረግ ዛሬ ቀላል ነው። ዕድሜ ለኦላይን ገበያ።
የዓለም ሀገራት ኑሯቸውን ያደረጉ ሰዎች በተለያዩ ወቅቶችና በዓላት የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም ወዳጆቻቸው ወደሚገኙበት ቦታ በመሄድ ጊዜን ያሳልፋሉ ። ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም ስጦታ የሚያበረክቱት አንድም በሚመጡበት ወቅት ያመጡትን በመስጠት ይሆናል። መምጣት ያልቻለ ሰው ደግሞ መልዕክቱ በትክክል ይደርስ ወይም አይደርስ ይሆን የሚል ጭንቀት ታክሎበትም ቢሆን ፖስታ ቤትን በአደራ መልዕክት አድራሽነት ይጠቀማሉ። ከዚህ ውጪ ሌሎች አማራጮች ብዙም አይታወቁም ነበር። ጊዜ ለሁሉም ነገር መፍትሄ አለውና አሁን ስጋትን የሚቀንስ የመረጡትን ስጦታ እቤት ድረስ የሚያደርስ አገልግሎት እደጃችን ደርሷል።
ራሔል ፍቅሬ በርቀት የሚገኙ ወዳጅ ዘመዶች ፣ ቤተሰቦች እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ በማንኛውም ወቅት ስጦታ እንዲለዋወጡ የሚያደርግ መፍትሄ ይዛ ቀርባለች። ስያሜው ‹‹ ቤተሰብ ጊፍትስ ›› ይሰኛል። የተለያዩ ሰዎች ፍላጎት ላይ ያተኮሩ ስጦታዎችን በቦታ ርቀት ምክንያት መስጠት ላልቻለ ሰው ልክ እንደባለቤት በመሆን የታዘዘውን ስጦታ ለተሰጪው ባለበት ያደርሳል ። ቤተሰብ ጊፍት የተቋቋመበት ዓላማ በርቀት የሚገኘውን ሰው ፍላጎት ለማሳካት፤ በተለያዩ ሁነቶች የታዘዟቸውን ስጦታዎች በሚፈለግበት ቀን ለታዘዘላቸው ሰዎች ማድረስ እና ለስጦታ ተቀባዩም ደስታን መፍጠር ነው።
እንዲህ ያለ የሥራ ሀሳብ እምብዛም በሀገራችን ያልተመደ በመሆኑ አጀማመሩ ምን ይመስል እንደነበር ራሔል እንዲህ ትገልጻለች። ‹‹ አብዛኛዎቹ ደንበኞቻችን ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ናቸው። የጀመርንበት ምክንያት በቅርብ የምናውቃቸው ከሀገር ውጪ የሚገኙ ሰዎች ለወዳጆቻቸው የዓመት በዓል ሲሆንና ለተለያየ ፕሮግራም ስጦታ መስጠት እየፈለጉ ነገር ግን መንገዱን ማግኘት ባለመቻላቸው ሲቸገሩ በማየታችን ነው ›› ትላለች። ራሔል በዚህ ዙሪያ ያለውን ክፍተት የሚሞላ በውጪው ዓለም ያለውን ተመክሮ በማየት ለሀገራችን አዲስ የሆነ ሀሳብ ይዛ ብቅ ብላለች።
የቤተሰብ ጊፍት ሰዎች ናፍቆታቸውን የሚወጡበትን፣ በአካል ቢኖሩ ለወዳጆቻቸው ማድረግ የሚፈልጉትን በውጭ ያሉ ወላጆች ለልጆቻቸው ልደት ፣ ለባለቤታቸው የጋብቻ በዓል፣ ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው የበዓል ስጦታ መስጠት ሲፈልጉ በዚህ የቤተሰብ ስጦታ አገልግሎት አማካኝነት የሚፈልጉትን የስጦታ አይነት ለሚፈልጉት ይልካሉ። ኧረ እንዳውም የመልካም ቀን ምኞታቸውን በስጦታ የታጀበ ማድረግ ከፈለጉ የቤተሰብ ጊፍትን እንደአማራጭ ይጠቀማሉ። ራሔል ለዚህ አገልግሎት ምቹ ሆኖ ያገኘችው ቤተሰብ ስጦታ የሚል ይፋዊ ድህረገጽ ነው። በሌሎች የማህበራዊ ገጾች እንዲሁ በመጠቀም ሰዎች የስጦታ ጥቅሎችን በማዘጋጀት እንዲሁም ደንበኞቻቸው የሚፈልጉትን ስጦታ በማካፈል ለሚፈለገው ሰው ባለበት ቦታ ያደርሳሉ።
የስጦታ ጥቅሎቹ የመልካም ቀን ምኞት፣ የበዓል ጥቅል በሀገራችን በስፋት በሚከበሩ የአዲስ አመት፣ ገና፣ የፋሲካ በዓል፣ ረመዳን ፤ ልደት፣ ሠርግ፣ የጋብቻ ዓመታዊ በዓል ያካትታል። በእነዚህ ሁነቶች ለስጦታ የሚቀርቡት አበባ፣ ልዩ ልዩ ጣፋጭ ምግቦች፣ የተለያዩ ስጦታዎች ናቸው። ለበዓላት ወቅት ደግሞ በግ፣ ዶሮ እና ሌሎች ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ግብዓቶችን በስጦታ መልክ ይቀርባሉ።
ከውጭ ሀገር የሚኖሩ ሰዎችን ትእዛዝ ተቀብሎ በሀገር ቤት ለሚገኙ ሰዎች ማድረስ መልካም ሀሳብ ቢሆንም ከሌሎች ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ያለው የክፍያ መንገድ አስቸጋሪ እንደነበር ራሔል ታስታውሳለች ። ” ይህንን ስራ በጀመርንበት ወቅት አስቸጋሪው የነበረው የክፍያ ስርዓት ነበር። እዛ ሀገር ያለ ሰው ወደዚህ ቀጥታ ክፍያ የሚከፍልበት መንገድ አልነበረም። በወቅቱ የነበረውም የክፍያ መንገድ ይቆያል። ክፍያ ካልተፈጸመልን ደግሞ አገልግሎቱን መስጠት ከባድ ነው። ›› በማለት የምትገልጸው ራሔል አሁን ግን እንደቴሌብር ባሉ የክፍያ አማራጮች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ባንኮች ቀጥታ ወደኢትዮጵያ ክፍያ መፈጸም የሚቻልባቸው አማራጮች መፈጠራቸውን ትናገራለች። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸው የራሔልን ስራ ቀላል አድርጎላታል።
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ቤተሰብ ጊፍትን በመጠቀም ስጦታቸውን ለወዳጆቻቸው ይልካሉ። ‹‹ ደንበኞቻችን በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ናቸው። በዱባይ፣ በአሜሪካ በፈረንሳይ፣ በጀርመን እና ሌሎች ሀገራት ላይ የሚገኙ ደንበኞች አሉን። የውጭ ሀገር ዜጎች ሆነው በኢትዮጵያ በስራ ላይ ያሉ ሰዎች ወይም ቤተሰቦቻቸውም በእኛ በኩል ስጦታ ይልካሉ። ›› በማለት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያሉ ደንበኞችን ፍላጎት እያረካች መሆኑን ትናገራለች።
አንድ ሰው ለወዳጁ ስጦታ ለመስጠት ሲያስብ ስለሚገዛው እቃ አስቀድሞ ያስባል። ወዳጄ ያስደስተዋል ያለውን የስጦታ አይነት ከመረጠ በኋላ የእቃው ጥራት ላይ እርግጠኛ መሆን ይገባል። ምክንያቱም ስጦታ የሚሰጠው ለሚወዱት ሰው ነውና። ‹‹ ለስጦታ የምንገዛቸውን እቃዎች የምንገዛባቸው ቋሚ አቅራቢዎች አሉን። በተቻለን መጠን በጣም ከሚታወቁ እና ስም ካላቸው አቅራቢዎች እንገዛለን። ›› በማለት የምታብራራው ራሔል በዚህ ወቅት ስጦታውን መስጠት የፈለጉ ደንበኞቻቸው ፍላጎት ምን እንደሆነ በቅድሚያ ይጠየቃሉ። ስጦታውን ካዘጋጁ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነ ያለምንም ክፍያ ስጦታው ለሚገባው ሰው በሰዓቱ ያደርሳሉ። ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ባሏቸው ኤጀንቶች አማካኝነት እንዲሁ በባህርዳር፣ ደብረዘይት፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ እና ሀዋሳ ላይ አገልግሎቱን ያቀርባሉ ።
በተለያየ መንገድ አገልግሎት የመስጠት ስራ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የደንበኞቻቸውን ፍላጎት በማሟላት ደንበኞቻቸው በሚሰጧቸው ምላሽ የስራቸውን ስኬታማነት ያረጋግጣሉ። የቤተሰብ ጊፍት ደግሞ ልክ እንደቤተሰብ በመሆኑ በሚሰጡት አገልግሎት ቤተሰብን ከቤተሰብ ያቀራርባሉ። ‹‹ ስጦታ ሲሰጥም ሆነ ስንቀበለው በጣም ደስ የሚል ነው። ሌሎች ሰዎች ደግሞ የፈለጉትን በማሳካት ለሰዎች ደስታ መፍጠር በጣም የሚያስደስት ስራ ነው። ›› በማለት ራሔል ስራዋን ትገልጻለች።
ራሔል በዚህ ስራዋ የሰዎችን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ በርካታ የስራ እድልን መፍጠር ችላለች። ‹‹ የምናቀርባቸውን ስጦታዎች የሚያቀርቡልን ደንበኞች አሉን። እነዛን ስጦታዎች ደግሞ አዘጋጅተን ለሚመለከተው ሰው ባለበት ቦታ የሚያደርሱልን ሰራተኞች አሉ። ስለዚህ ለብዙ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ችለናል ብዬ አስባለሁ። ›› ትላለች።
የቤተሰብ ጊፍት ከተመሰረተ ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ሰዎች ስጦታዎችን ለማዘዝ ይፋዊ ድህረ ገጽ እና ሌሎች አማራጭ የማህበራዊ ገጾችን በመጠቀም ይስተናገዳሉ። እንደቤተሰብ ጊፍት ለማሳካት የሚፈልጓቸው እቅዶች እንዲሁ አሉ። ‹‹ አሁን ላይ እያስተናገድን ያለነው ከውጭ ሀገር ከሚገኙ ደንበኞቻችን ጋር ነው ። በሀገር ውስጥ ያሉ ደንበኞችን ማሳተፍ እንፈልጋለን ። ወደፊት የራሳችንን የስጦታ ስፍራ ገንብተን ሰዎች ራሳቸው መጥተው የሚፈልጓቸውን ስጦታዎች መርጠው በሚፈልጉት መንገድ አዘጋጅተው እንዲወስዱ የማድረግ ሀሳብ አለን። ለዚህም ስራ ሰፊ የሆነ ቦታ ያስፈልጋል። ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል አስፈላጊው ድጋፍ በዚህ በኩል ቢደርግልን የሚል ሀሳብ አለን። ››
ራሔል ይህን ስራ የጀመረችው በአካባቢዋ ባስተዋለችው በሰዎች ፍላጎት እንደሆነ በማስታወስ የራሳቸውን ስራ መስራት ለሚፈልጉ ወጣቶችም ሆነ ሴቶች ተሞክሮዋን ታጋራለች። ‹‹ ስራ ፈጣሪ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች መጀመሪያ አካባቢያቸውን ማስተዋል፤ ሰዎች እንደችግር የሚያነሱትን ነገር ትኩረት ሰጥተው ማዳመጥ አለባቸው። ዋናው ነገር ስራውን መጀመር ቢሆንም በቀጣይ ደግሞ ስራው ስኬታማና ተመራጭ እንዲሆን ዋጋ መክፈል፣ በቂ ጊዜ መስጠት አለባቸው። ›› በማለት አብዛኛዎቹ ሰዎች የሥራ ሀሳብ ኖሯቸው ቢጀምሩትም ለሥራው የሚገባውን ጥረት ባለማድረጋቸው ብዙም ሳይቆዩ እንደሚያቋርጡት ትገልጻለች። ‹‹ በሀገራችን በርካታ ወደሥራ መቀየር የሚችሉ ፤ መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮች ስላሉ መፍትሄውን ፈጥረው ለመስራት ፍቃደኛ ከሆኑ መለወጥ ይችላሉ ። ” ዋናው ውስጣዊ የሥራ ተነሳሽነት መኖር መሆኑን ትናገራለች።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም