ጂንካ:- ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የአሪ ዞን አስታወቀ።
አሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሪ ዞን በግብርናው ዘርፍ ብዙ ጸጋዎች አሏት። በዋናነት ቡና፣ ኮረሪማና ቀይ ቦሎቄና ሌሎች ምርቶች በስፋት የሚመረቱበት ዞን ነው። የተለያዩ ሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት እየተጠቀምን ነው ብለዋል። እንዲሁም የክልሉ የግብርና ምርምር ማእከል የምርምር ስራዎችን በመስራት የቁም እንስሳት ውጤታማነትን የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፣ በአሪ ዞን ላይ እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂና የተሻሻሉ የሩዝ፣ በቆሎ፣ ስንዴ እና አደንጓሬ የዘር ብዜት ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በግብርናው ዘርፍ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራዎች ህብረተሰቡን በማስተባበር ባለፉት ጊዜያት የተሰሩ ስራዎች እጅግ አመርቂ ውጤት አምጥተዋል። የግል አልሚዎች በግብርናው ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፤ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምድ እያደገ መጥቷል። በግብርና በእርሻ ዘርፍ በግብርና ማቀነባበሪያ ለሚሰማሩ አልሚዎች በዞኑ በበቂ ሁኔታ የተዘጋጁ መሬቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች በተቀላጠፈ ሁኔታ የመሬት አቅርቦት እየተዘጋጀ ነው ያሉት አቶ አብረሃም፣ በዞኑ ውስጥ ለኢንቨስትመንቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መሰረተ ልማቶች የማስፋት ስራዎች እየተሰሩ ነው። ዞኑ ከግብርና ጐን ለጐን ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ መዳረሻ በመሆኑ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ መሰማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ዞኑ ዝግጁ ነው ብለዋል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋየ በበኩላቸው፣ ዞኑ አዲስ እንደመሆኑ የምርጥ ዘር ችግር ነበረበት። ይህን ችግር ለመቅረፍ ከአርሶ አደሮች ጋር በመሆን የሩዝ፣ በቆሎ፣ ስንዴና የአደንጓሬ ዘር በኩታ ገጠም የብዜት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። የበቆሎ የምርጥ ዘር ማባዣው ጣቢያ በኩታ ገጠም በ15 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፣ ዞኑን በግብርና እራሱን ለማስቻል ያግዛል።
በአሪ ዞን ከበቆሎ ምርጥ ዘር ማባዣ ጐን ለጐን በ75 ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር ማባዣ ጣቢያ አለ ያሉት የግብርና ቢሮ ኃላፊው፤ በቀጣይ የዞኑ አርሶ አደሮች በሁሉም የሰብል አይነቶች የምርጥ ዘር ችግር እንዳይገጥማቸው እየተሰራ ነው። የዘር አቅርቦት ችግርን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም