በአዲስ አበባ 154 ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ ነው

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ 154 ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ እንደሚገኝ የከተማው ህብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኔዘርላንድ የተደረገውን የህብረት ሥራ ማህበራት የሥራ ጉብኝት ተከትሎ በከተማው ከሚገኙ ህብረት ሥራ ማህበራት፣ዩኒየኖችና ሠራተኞች ጋር የፓናል ውይይት ትናንት ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ 154 የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት የኑሮ ውድነትን የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ ነው፡፡

የከተማው ህብረት ሥራ ኮሚሽን ዘጠኝ ሺህ ማህበራት ያሉት ሲሆን፤ አንድ ሺህ 600 የቁጠባ ማህበራት መሆናቸውን የገለጹት ኮሚሽነሯ፤154 የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራትና 11 ዩኒየኖች በከተማው የተለያዩ ምርቶችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ መረጋጋት ሥራ እየሠሩ ይገኛል ብለዋል፡፡

ማህበራቱ የትኩረት አቅጣጫቸው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት መሆኑን ጠቅሰው፤ በማምረትና እሴት ጨምሮ መሥራት ላይ ቀሪ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

የህብረት ሥራ ማህበራት ምርትን ከአምራቹ በቀጥታ በማምጣት ከነጋዴው በቀነሰ መልኩ ለህብረተሰቡ እንደሚያቀርቡ ገልጸው፤ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን ከነጋዴው በዋጋ በቀነሰ መልኩ እያቀረቡ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በእሁድ ገበያዎች ላይ አምራቾች፣ማህበራት፣ነጋዴዎች ምርቶችን እያቀረቡ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነር ልዕልቲ፣በእሁድ ገበያ ተደራሽነትን ማስፋትና የአቅርቦት አማራጭን የማብዛት ሥራ በመሥራት ህብረተሰቡን

ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ በ800 የመቸርቸሪያ ሱቆች ላይ የሚቀርቡ የተወሰኑ ምርቶች ላይ ከእሁድ ገበያ ዋጋ ለውጥ ሊኖራቸው እንደሚችል ጠቅሰው፣ማህበራቱ ለህብረተሰቡ አማራጭ ገበያ ሆነው መቅረባቸውና የግብርና ምርቶች በሱቆችና ወፍጮ ቤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የህብረት ሥራ ማህበራት የዘመኑ አሠራር ሥርዓትን በመዘርጋት ለማህበረሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው በመግለጽ፤ የውስጥ አቅምን በመጠቀም ወደ አምራችነት መሸጋገር፣ተደራሽነትን ማስፋትና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

የህብረት ሥራ ማህበራት ግላዊ ጥቅም ማካበቻ ሳይሆኑ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣የከተማ አስተዳደሩ ለማህበራቱ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የአሰራር ሥርዓቶችን ማስተካከሉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ሙመድ በበኩላቸው፣ኮሚሽኑ ለማህበራቱ የአሰራር ሥርዓቶችን፣ፖሊሲን፣ስትራቴጂን፣ገበያ የማፈላለግ፣ አቅም ግንባታና የውጭ ተሞክሮዎችን የማስፋት ሥራዎችን ይሠራል፡፡

ኔዘርላንድ በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ከድህነት ወደ ብልጽግና መሸጋገር ችለዋል ያሉት አቶ አብዲ፤ በሀገሪቱ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ እንደሀገሪቱ ሁኔታ ወደ ተጨባጭ ሁኔታ በመለወጥ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያላትን የተሻለ የተፈጥሮ ጸጋ ፣አምራች ሀይልና ሌሎች መልካም እድሎች መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ማህበራትን በማጠናከር ለዜጎችና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You