አዳራሹ በሰው ተሞልቷል፤ በርከት ያለው ሰው የዕለቱን “ክብር ለጥበብ የተሰኘ መርሃግብር” እንዲከታተል የተጋበዘ ሲሆን፣ በቁጥር ጥቂት የሆነው ደግሞ ለሽልማት በበቃው የተለያየ የሙያ ዘርፍ አንዱ በሆነው በሰራው የላቀ ስራ ተመርጦ እውቅና ሊሰጠው የታደመ ነው። ለሽልማት ከበቁ የሙያ ዘርፎች መካከል ደግሞ ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ሰርከስ እና ሌሎች የጥበብ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው። በአብላጫነት የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ አካላት የዕለቱን ሽልማት ለመቀበል ችለዋል።
ይህ ሰሞኑን በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት የቀረበው አራተኛው ክብር ለጥበብ የተሰኘ መርሃ ግብር ድንቅ ስራ ለሰሩ የኪነ ጥበብ ሰዎች ዕውቅናና ሽልማት የሰጠ ሲሆን፣ መርሃ ግብሩ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ 67 ተሸላሚዎች መመረጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፤ ሌሎች ስድስት ልዩ ተሸላሚዎች ደግሞ የክብር ዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በዕለቱ ከተሸለሙት መካከል ቀሲስ ረዳኢ ኃይሉ አንዱ ናቸው፤ የመጡበት አካባቢ ትግራይ ክልል መቐለ፣ ኲሐ ክፍለ ከተማ መሆኑን ይናገራሉ። ቀሲስ፣ ለሽልማት ያበቃቸው ስራ ጥንታዊ እደ ጥበብ የሆነው የሽመና ስራ መሆኑን ያስረዳሉ።
ከገጠር ወደ ከተማ ትምህርት ለመማር እና የበለጠ ኑሮ ለማሻሻል መምጣታቸውን የገለጹልን ቀሲስ ረዳኢ፣ ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ በመንግሥት መስሪያ ቤት ተቀጥረው ቢሰሩም፤ ውስጣቸው የነበረው የሽመና ጥበብ ፍላጎት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በፍቅር የሚሰሩት ስራ መሆኑን ያስረዳሉ።
እርሳቸው የሚሰሩት የሽመና አልባሳት በእንደርታ እና በራያ አካባቢ የሚለበስ የባህል ልብስ ቦፌ፣ድርበድር፣ ዝርዝር፣ ፈትል እና ሌሎች በርካታ ባህላዊ አልባሳት ጥበብ በማላበስ እና አዳዲስ ፈጠራዎችን በመጨመር ለገበያ እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ።
ቀሲስ ረዳኢ፣ መንፈሴ እየተደሰተ ከሙያው በማገኘው ገቢ ምድራዊ ለሆነው ኑሮዬ እጅግ አስፈላጊ የተባሉት ነገሮች ማለትም ዘመናዊ ቤትና መኪና ገዝቻለሁ ይላሉ። የመጀመሪያ ልጃቸው ሙያውን አስተምረውት የአምስት ዓመት ዕቅድ በማውጣት የራሱ መኪና መግዛቱን ይናገራሉ። እንዲሁም ሌሎች ተቀጥረው እየሰሩ እንዲጠቀሙ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውንም ያስረዳሉ።
“መንፈስ እና ስጋ ማዋደድ የሚቻለው በጥበብ ነው።” ያሉት ቀሲስ ረዳኢ፤ ስጋችን ከመንፈሳችን ጋር ሚዛን አስጠብቀን በመታዘዝ ድንቅ የሆነ አዳዲስ ፈጠራ በተደጋጋሚ እና በዘላቂነት ስንተገብር የኪነ ጥበብ ዋነኛ ምልክት መሆኑን ለማወቅ እምነታችን ያስረዳናል ይላሉ።
ከመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መካከል ቅዱስ ጳውሎስ፤ ‘ሊሰራ የማይወድ ቢኖር አይብላ’ ይላል ያሉት ቀሲሱ፣በቤተ መቅደስ እና በሌሎች ተቋማት ተቀጥሬ ከምጠብቀው ወርሃዊ ደመወዝ ይልቅ በነፃነት እና በደስታ የምሰራው የጥበብ ሙያ እጅጉን ይበልጥብኛል ሲሉ ይናገራሉ። መርሃ ግብሩ ላይ ለተደረገላቸው የሽልማት እና የዕውቅና ስጦታ እጅጉን መደሰታቸውንም ይገልፃሉ።
ኪነ ጥበብ ለሀገር እድገት ዋነኛው ነው ያሉ ሲሆን፤ ሰርተን በምናገኘው ገቢ ግብር ለሀገር መክፈል ያስደስተኛል ሲሉ ያስረዳሉ፤ በመሆኑም ለረጅም ዓመታት ግብር መክፈል በሚጀመርበት ቀን ሐምሌ አንድ ቁጥር አንድ የመጀመሪያው ግብር ከፋይ እርሳቸው መሆናቸውን በኩራት ይናገራሉ።
በተመሳሳይ በዚሁ መርሃ ግብር ልዩ ተሸላሚ ከሆኑት መካከል በማስታወቂያ ስራ ለረጅም ጊዜ ታዋቂነትን እና ተወዳጅነትን ያተረፉት አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ እና ሙሉአለም ታደሰ ተጠቃሽ ናቸው። አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝቶ ሽልማቱን ተቀብሏ። በተደረገው የዕውቅና እና የሽልማት ስጦታ እጅግ መደሰቱን ገልጿል። እስከ ዛሬ በማስታወቂያ ዘርፍ የዕውቅና ሽልማት ሳይደረግ አሁን መደረጉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሊመሰገን እንደሚገባው ተናግሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፣ ለታዳሚዎች እና ለተሸላሚዎች የጥበብን ታላቅነት ገልጸዋል። ሚኒስትሯ፣ ለጥበብ ክብርም ትኩረትም እንደሚሰጠው አስረድተዋል። በሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘን ለሚገኙ የኪነ ጥበብ ሰዎች እና የጥበብ ወዳጆች የኪነጥበብ ዘርፍ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለማጠናከር ሙያዊ ተሳትፎ ሊጠነክር እንደሚገባም አመልክተዋል።
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ዘርፈ ብዙ ባለሙያዎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እና ሌሎች የጥበብ ስራዎች በአብላጫነት ያሳዩ ተሸላሚዎች ሽልማታቸውን ወስደዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም