የፊልም ዘርፉ የሀገር ዋልታና ማገር እንዲሆን

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ምንም እንኳ የተለያየ ስሜትና ፍላጎት ቢኖረውም የሀገር ህልውና የሚፈታተኑ ሴራዎችን በማክሸፍ የኢትዮጵያን ሰላምና ክብር ማስጠበቅ የጋራ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። ኪነ-ጥበብ የሕዝብ አንደበት እንደሆነ ሁሉ የፊልም ዘርፉም የሀገር ዋልታና ማገር ሆኖ እንዲያገለግል መስራት ያስፈልጋል።

ፊልም ባህልን ፣ ትውፊትን ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ ይጠቅማል። በተለይ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ኮሪያና ሌሎች በፊልም ኢንዱስትሪው ውጤታማ የሆኑ ሀገራት የዓለምን መጻኢ እጣ ፈንታ በፊልም እንዲንጸባረቅ በማድረግ የሀገራቸውን ገጸታ ከመገንባት ባሻገር ከፍተኛ ገቢ ሲያገኙበት ይስተዋላል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሚኔቶ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የፊልም ዘርፉ ባለሙያዎች በሀገራዊ ክብር ቁርጠኛ በመሆን የኢትዮጵያዊነትን ልዩ ገጸታ ማሳየት አለባቸው። ይህም ማህበራዊ ቀውስን ለማስወገድ፣ አንድነትንና ሰላምን ለማጽናትና መልካም ገጽታን ለተቀረው ዓለም ለማሳየት ጉልህ ድርሻ አላቸው።

ዘርፉን ለትውልድ እድገትና ለሀገር ግንባታ መጠቀም ያስፈልጋል። ይህም ባህል፣ እሴት፣ አንድነት እና ሰላምን ከመጠበቅ አንጻር ከፍተኛ ሚና አለው ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የፊልም ዘርፉ ያለውን አወንታዊ ሚና አሟጦ ለመጠቀም በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፊልም የኅብረተሰቡን እሴት ወደ ተንቀሳቃሽ ምስል ተቀይሮ የሚቀርብበት ነው። ለምሳሌ ድህነት የኅብረተሰቡ ዐብይ ችግር ከሆነ እንዴት ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳያል ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሃሳቦችን ይዘው የሚሰሩ ፊልሞች ለሀገር ግንባታ ወሳኝነት አላቸው ብለዋል።

የአሜሪካ፣ የህንድና የሌሎች ሀገራት ፊልሞች ገቢን በማስገኘትና ኅብረተሰብን በመቅረፅ ረገድ ያላቸው ሚና ትልቅ መሆኑን ገልጸው፤ የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ በሚጠበቅበት ደረጃ ልክ እንዲያድግ የዘርፉ ባለሙያዎች የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመቅሰም ዘርፉን ማሳደግ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

ፊልምን ለሀገር ግንባታ ለማዋል መሰጠትን ይጠይቃል። የሀገር ቁጭት በውስጥህ ካለ በርካታ ለፊልም የሚሆኑ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ የዜጎች አንድነት፣ መተማመን፣ መፋቀርና ህብረትን የመመስረት ጉዳይ ድንቅ ፊልም ለመስራት ያስችላል ነው ያሉት።

ሀገር ግንባታ ውስጣዊነትን ይጠይቃልና ኃላፊነት በተሰማው መንገድ ከተሠራ ሀገር መለወጥ ይቻላል። በዚህ ረገድ ድርጅቱ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ልምዶችን የማስተላለፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በትብብር የመሥራት ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።

ሕዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም የዛሬ 34 ዓመት የተሰራው “አስቴር” ፊልም ከ35 ሚሜ ተንቀሳቃሽ ምስል ወደ ዲጂታል ፊልም ተቀይሮ በከንቲባ አዳነች አቤቤ ተመርቆ ለዕይታ በቅቷል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ጥበብ የእድገታችን እና የታሪካችን ማሳያ በመሆኑ በሀገር ግንባታና በማህበራዊ ህይወታችን ውስጥ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ አድርጎ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ጥበብ ትናንትን ከዛሬ ጋር ማያያዝ ይችላል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ “አስቴር” የተሰኘውን ፊልም ከዛሬ ህይወታችን ጋር እያስተሳሰርን ማየት አለብን። በዚህም ከትናንት ስህተት መማርና ጠንካራ ጎኖችን ደግሞ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በ1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን አማካኝነት ሀገራዊ ዘውግ ላይ ተንተርሶ የተሰራውና “አስቴር” የተሰኘው ኢትዮጵያዊ ፊልም፣ የአጻጻፍ ደረጃው ከፍ ያለና ከድርሰት እስከ ፕሮዳክሽን ድረስ ሙሉ በሙሉ በሀገር ባለሙያዎች የተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ከንቲባ አዳነች ገለጻ፤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በዓድዋ ሲኒማ በሀገራችን የመጀመሪያውን ባለ ቀለም ፊልም “አስቴር “የተሰኘውን ዲጂታላይዝ በማድረግ የሀገራችን አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ተጋባዥ እንግዶች በታደሙበት በይፋ መርቀን ከፍተናል ነው ያሉት።

ጥበብ ሀገርን በማነፅ ጉዞ ውስጥ አይነተኛ ሚና አላት። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ዘርፉ የሀገራችንን የልዕልና ጉዞ ሊያሳልጥ እንዲችል የኪነ-ጥበብ መሰረተ ልማቶችን ገንብቶ ለሕዝቡ ጥቅም አቅርቧል። ይበልጥ የማስፋፋቱን ስራም አጠናክረን የምናስቀጥል ይሆናልም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቢሮው የፊልም ሥራዎችን ከሦስት ዓመታት ወዲህ ከሀገር ውጭና በሀገር ውስጥ በማፈላለግ ዲጂታላይዝድ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቆየት ባሉ ፊልሞች የቀደመውን ማህበረሰብ የባህል ትስስር ለመዳሰስና ዛሬ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመለየት እንደሚረዱ ገልጸው፤ ቢሮው ከዚህ በፊት የመጀመሪያውን ባለ ነጭና ጥቁር ቀለም “ሒሩት አባቷ ማነው?” የተሰኘ ፊልም በድጋሚ ለዕይታ እንዲበቃ ለሲኒማ ቤቶች አስተዳደር አስረክቧል ብለዋል።

“አስቴር” ፊልም የአንድ ወጣ ሴት የህይወት ውጣ ውረድ የሚያሳይ ፊልም ነው። ፊልሙ በዘመኑ በተለያየ የኑሮና የትምህርት ደረጃ ያሉ የትዳር አጋሮች የሚደርስባቸው ጫናን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ፊልሙ ከ35 ሚሊሜትር በቀላሉ ከዘመኑ ጋር እንዲሄድ ተደርጎ ለትውልድ እንዲተላለፍ ተደርጓል።

በቀጣይ ፊልሙ በመንግሥት ሲኒማ ቤቶች ለዕይታ ከበቃ በኋላ በሀገራችን በተለያዩ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በውጭ ሀገር በተለያዩ ከተሞች ለዕይታ ይቀርባል። ለኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ እንደ አንድ የመሰረት ድንጋይ የሚታሰበው “አስቴር” ፊልም በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን የተሰራ ነው።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You