‹‹ በመንግሥት የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የታየው አመርቂ ውጤት በግሉ ዘርፍም እየተደገመ ነው ›› – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- በመንግሥት የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ የታየው አመርቂ ውጤት በግሉ ዘርፍም እየተደገመ መሆኑን የሚያሳዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቃቂ ቃሊቲ በተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያደረጉትን ጉብኝት አስ መልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ሰርቶ በማጠናቀቅ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ይህ ልምድ ከመንግሥት ፕሮጀክቶች አልፎ በግል ዘርፉም ከፍ ያለ ሥራ በመሥራት፣ በጥራትና በፍጥነት ሥራዎችን በማጠናቀቅ እየተደገመ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እምቅ አቅም ያላት ትልቅ ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሚጠበቅብን ያላትን አቅም ማወቅና ጥቅም ላይ ማዋል ነው፡፡ይህም የምናልማትንና የምናስባትን ኢትዮጵያ ለልጆቻችን ለማስረከብ በር የሚከፍት ነው ፡፡መልካም ልምዶችን ማጠናከርና በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ምርታማነት ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ልማታችንን ከግብ ለማድረስ እና ኢኮኖሚያችንን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና ይጫወታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የግል ዘርፉ ከሌብነት፣ በአቋራጭ ለመክበር ከመሞከርና ግብር ከመሰወር ወጥቶ ትልልቅ ሥራዎች ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ በዚህም ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ የሚጠበቅበትን አወንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለሀብቶች እና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ሀገር የሚለውጥ ሥራ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት በአምራች ዘርፉ እንዲደገም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ህልማችን ትልቅ ነገር እያሰብን ከትንሹ ተነስተን በፍጥነት ትልቁ ላይ መድረስ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን የጀመርንበትና የሠራንበት ሁኔታ ችግር ያለበት ነው፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችንም አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ እዳ አለባቸው፡፡ ይህን ሁኔታ መቀየርና በሀገር አቅም ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ያሳዩ ባለሀብቶችን ልምድ አስፍቶ መሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው፡፡ ሀገራዊ ጥቅል ምርት በአምስት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ አድጓል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሀራ በታች በሚገኙ አፍሪካ ሀገሮች ትልቁ ኢኮኖሚ ሆኗል፡፡ይህም የኢትዮጵያ የመነሳት ጊዜ እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክት ነው፡፡

ሁላችንም በትብብር ያለንን አቅም አስተባብረን ሀገር የሚቀይርና ለብዙዎች የሥራ እድል የሚፈጥር ሥራ ለመሥራት መትጋት እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You