ጨካኙ የትዳር አጋር

ዘፀዓት ተወልደ ሐጎስ 34 ዓመቱ ነው:: አስመራ የተወለደው ዘፀዓት እንደልጅ ተሞላቆ አላደገም:: ዘመኑን ያሳለፈው በመከፋት ውስጥ ሆኖ ነው:: ማንንም አያምንም:: አቶ ተወልደ ሐጎስ እና ወይዘሮ ፀሐይ ገብረመድሕን እናሳድገዋለን ብለው ቢወልዱትም አልሆነላቸውም:: አሥር ዓመት ሲሞላው ከቤተሰቦቹ የሚለይበት አጋጣሚ ተፈጠረ:: ኤስ ኦ ኤስ በተሰኘ የሕፃናት ማሳደጊያ በመግባቱ የእናት እና አባት ጠዓምን ሳያውቅ አደገ::

በትምህርት ብዙም ያልዘለቀው ዘፀዓት፤ 18 ዓመት ሲሞላው እንደእኩዮቹ ዩኒቨርሲቲ አልገባም:: የሕፃናት ማሳደጊያው ደግሞ ‹‹ዕድሜህ ደርሷል›› ብሎ ከማሳደጊያው አስወጣው:: ዘፀአትን የሚያስጠጋው፤ የሚያሳድረው እና የሚያበላው አልነበረም:: ዘመድ የለውምና መቀሌ ከተማ ጎዳና ላይ መኖር ጀመረ:: በእዚህ የተነሳ ማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አለው::

ምንም እንኳ ያአገሩ ሰዎች ባይረዱትም፤ ጎዳና ላይ ከወጣ በኋላ በአጋጣሚ ሌላ ዕድል አገኘ:: ከአንዲት ፈረንጅ ጋር አገናኝተውት ከአሜሪካ በየወሩ 300 ዶላር እየላከችለት መኖሩን ቀጠለ:: ይሄ የሕይወት መስመሩ እንዲስተካከል ረዳው:: ዘፀዓት ራሱ እንደሚናገረው፤ ብዙውን ጊዜ ለሰዎች ጥሩ ስሜት የለውም:: ምክንያቱ ደግሞ ማንም ለእኔ ፍቅር የለውም የሚል እምነት ስላለው ነው:: ‹‹ሰዎች እንኳ የሚጠጉኝ የምጠቅማቸው ከሆነ ብቻ ነው::›› ይላል::

ዘፀዓት ከጎዳና ላይ ተነስቶ ገንዘብ እያገኘ መኖር ሲጀምር የሥራ ዕድል አገኘ:: በትግራይ ክልል የምሥራቃዊ ዞን የፀጥታ ዘርፍ ሥር ተቀጠረ:: ወንደ ላጤ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ የሌለው ብቸኛ ሆኖ ኑሮውን ሲገፋ የቆየው ዘፀዓት፤ ፍቅረኛ መፈለግ ጀመረ:: አብራው የምታድግ እና አብራው በዘላቂነት የምትኖር ፍቅረኛ በመፈለጉ የሚመኛትን አገኘ:: ሉዋም ውበት ከተባለች ውብ ወጣት ጋር በፍቅር ወደቀ::

ፍቅር አላውቅም የሚለው ዘፀዓት ሉዋምን አብዝቶ ወደዳት:: ኑሮውም እያደገ የሬስቶራንት ባለቤት እስከ መሆን ደረሰ:: ሥራው እየተሳካለት ሲሔድ ከሉዋም ጋር ጋብቻ መሠረቱ:: ከእርሷ አልፎ ቤተሰቦቿን መደጎም ጀመረ:: በእርሷ ብቻ ሳይሆን በቤተሰቦቿም ተወዳጅነትን አተረፈ::

ትዳር

ዘፀዓት እና ሉዋም በ2011 ዓ.ም ትዳር መስርተው መኖር ሲጀምሩ ቤታቸው በደስታ የተሞላ ነበር:: ወንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ግን መጨቃጨቅ ጀመሩ:: ሁለቱም ከአስመራ የመጡ አብረው ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ለመኖር ተግባብተው ተማምነው እና ተማምለው ትዳር ቢመሰርቱም፤ ሁለቱም ብዙም ሳይቆዩ ዘፀዓትም ‹‹ከእርሷ ጋር መኖር አልፈልግም፤›› ሉዋምም ፤ ‹‹ከእርሱ ጋር መኖር አልፈልግም›› መባባል ጀመሩ::

የሉዋም አባትም ሆኑ ወንድም እህቶቿ ሁሉም ጭንቀት ውስጥ ገቡ:: በኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም ጦርነት በነበረበት ጊዜ እነርሱ የሚኖሩት ትግራይ ነበር:: ዘፀዓት ውቅሮ ውስጥ ሬስቶራንት ከፍቶ እየሠራ ነበር:: ዘፀዓት እንደሚናገረው፤ በወቅቱ የነበረው የውቅሮ ከተማ ከንቲባ ሬስቶራንትህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ይወሰዳል ብሎ ሃብቱን ቀማው::

ለልጁም ሆነ ለሚስቱ የሚያወጣውን ወጪ እያሳሰበው የመጣው ዘፀዓት፤ የያዘውን ይዞ አዲስ አበባ ለመግባት እና ሌላ ሥራ ለመሥራት አሰበ:: ነገር ግን ሉዋም ፍቃደኛ አልሆነችም፤ ዘፀዓት አዲስ አበባ ለመግባት መቁረጡን እርሷ እምቢ ካለች ልጁን ይዞ እንደሚሔድ ነገራት:: ሉዋም በፍፁም አዲስ አበባ መሔድ እንደማትፈልግ ተናገረች:: ዘፀዓት ያሰበውን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልምና ልጁን ይዞ አዲስ አበባ ገባ:: ያለ እናት ድጋፍ ልጁን ማሳደጉን ቀጠለ::

ዘፀዓት አዲስ አበባ ሲገባ የተቀበለችው የሉዋም እህት ነበረች:: ሁኔታዎችን አመቻችቶ ቤት ተከራይቶ ልጁን ይዞ መኖሩን ቀጠለ:: ሕይወትን ለብቻው ለመግፋት ቢወድም የሚሆን አልነበረም:: የሉዋም ቤተሰቦች ‹‹እባክህ ከእርሷ አትለይ፤ አብርሃት ኑር::›› እያሉ አስጨነቁት:: በተለይ የሉዋም አባት ከትግራይ እየደወሉ፤ ‹‹ ልጄ እባክህ አብራችሁ በሰላም ልጃችሁን አሳድጉ›› ሲሉ ተማፀኑት:: ወንድሟ እስክንድር ታህሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ፤ ‹‹ሉዋም ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች:: አብራችሁ በሰላም ብትኖሩ ይሻላል፤ ይዣት ልምጣ ወይ ?›› ሲል በስልክ ጠየቀው::

ዘፀዓት ከሉዋም ጋር የመኖር ብዙም ፍላጎት ባይኖረውም፤ ልመናቸውን ሰምቶ እንድትመጣ ተስማማ:: ሉዋም መፍቀዱን ስታውቅ ስልክ ደውላ ‹‹እህቴም ስላለች ለሶስታችንም የትራንስፖርት ገንዘብ ላክልን::›› አለችው:: ዘፀዓት ገንዘብ ላከ:: ዘመኑ 2013 ዓ.ም በመሆኑ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ መግባት ቀላል አልነበረም:: ዘፀዓት ሰባት ሺህ ብር ከፍሎ መኪና ተከራይቶ ግማሽ መንገድ ድረስ ሔዶ ሚስቱን ከወንድም እና እህቷ ጋር አዲስ አበባ እንዲገቡ አገዛቸው::

ቦሌ አካባቢ ቤት የተከራየው ዘፀዓት፤ ይዟቸው ወደ ቤቱ ገባ:: ሉዋም ልጇን እንዳገኘችው እንዲያቅፋት እና እንዲስማት ፈለገች:: የአንድ ዓመቱ ከስድስት ወር ዕድሜ ያለው ህፃን ግን ሊጠጋት አልፈለገም:: ሉዋም ተበሳጨች፤ ዘፀዓትን ‹‹ያንተ ሥራ ነው ስትል›› ወቀሰችው:: ዘፀዓት ምንም አላላትም:: እንግዳ በመኖሩ ጭቅጭቅ ተፈጥሮ ነገሩ ሳይጋጋል ቀረ:: በዕለቱ ሁሉም በአንድነት በሰላም ዘፀዓት ቤት አደሩ::

በማግስቱ ዘፀዓት ሁሉንም ሆቴል ወስዶ ጋበዛቸው:: ከዛ በኋላ ግን እህት እና ወንድሞቿ ወደየሚሔዱበት ሄዱ:: ዘፀዓት እና ሉዋም ልጃቸውን ይዘው አብረው መኖር ጀመሩ:: ሆኖም ኑሯቸው በጭቅጭቅ የተሞላ ነበር:: ጠባቸው ከልጃቸው አልፎ አከራዮቻቸውን መበጥበጥ ጀመረ:: በኋላ በኋላ ሉዋም ለዘፀዓት፤ ‹‹ ጓደኞችህ በረሃ ናቸው:: አንተም በረሃ ግባ::›› እያለች መጨቃጨቅ ጀመረች:: የታህሳስ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጠባቸው ደግሞ የተለየ ነበር::

የዘፀዓት እና የሉዋም ጠባቸው የከረረ በመሆኑ ጩኸታቸውን አከራዮቻቸው ሰሙ:: ‹‹እባካችሁ ለምን ተስማምታችሁ አትኖሩም? በትዳር የሚኖረው ተቻችሎ ነው::›› ብለው ለማስታረቅ ሞከሩ:: በማግስቱ ማለትም በታህሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ወንድሟ ለዘፀዓት ደውሎ ላግኝህ አለው::

የሉዋም ወንድም ዘፀዓትን የጠራው ‹‹አብረን ወደ መቀሌ እንሂድ›› ለማለት ነበር:: ዘፀዓት ግን መቀሌ መሔድ እንደማይፈልግ ሲገልፅለት የሉዋም ወንድም ‹‹ትናንትም ከሉዋም ጋር ተጣልታችሁ ነበር:: እርሷ ከአንተ ጋር መኖር አትፈልግም:: ከአንተ ተለይታ ልጇን ይዛ ለመኖር እየተዘጋጀች ነው::›› ሲል ነገረው:: ወንድሟን በደንብ ያዳመጠው ዘፀዓት ወደ ቤቱ ሔደ::

ያቺ ጊዜ

ዘፀዓት እንደተናገረው፤ ከወንድሟ የሰማውን ወሬ እንዳልሰማ መስሎ ቤቱ አደረ:: በማግስቱ ጠዋት ሊያነጋግራት ሞከረ፤ ሆኖም ዕድል አልሰጠችውም:: ስድስት ሰዓት አካባቢ ሶፋ ላይ ጋደም ብሎ እንደተኛ ሉዋም አንገቱን አነቀችው:: አንገቱን ሲያስለቅቃት ከጠረጴዛ ላይ ቢላዋ አንስታ ልትወጋው ስትል ቢላዋውን ነጥቆ ደረቷን ወጋት፤ በድጋሚ ቢላዋውን አንገቷ ላይ አሳረፈው:: በቀኝ በኩል ብቻ ሳይሆን በግራ በኩልም ስለቱን አንገቷ ላይ ሲያጋድመው ሉዋም ወደቀች::

ደሟ የሚፈሰውን ሉዋምን ጥሎ ልጁን አንጠልጥሎ በሩን ዘግቶ ቁልፉን እዛው በሩ ላይ ትቶ እየሮጠ ከጊቢው ወጣ:: ማንም አላየውም ነበር:: ሉዋምም ላትመለስ በዛው አሸለበች:: ዘፀዓት ከአካባቢው ተሰወረ:: ድርጊቱን ፈፅሞ ለመሰወር ሲያስብ ወዲው በአዕምሮ የመጣችው አዳማ ናት:: ከአዲስ አበባ ወጥቶ ወደ አዳማ ሄደ:: በዚሁ ትዳራቸው በገዳይ እና ሟችነት ተቋጨ::

በማግስቱ አላስችል ሲለው አከራዮቹ ጋር ደወለ:: የሉዋምን ሁኔታ ሲጠይቅ መሞቷ ተነገረው:: ዘፀዓት ብዙ አልቆየም ተመልሶ አዲስ አበባ በመምጣት እጁን ለፖሊስ ሰጠ:: የ34 ዓመት ዕድሜ ያለው ዘፀዓት የልጁን እናት ሉዋምን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደሉ መፀፀቱን ገለፀ:: ፖሊስም ምርመራውን አጠናቆ ክስ እንዲመሠረት ለዐቃቤ ሕግ አቀረበ::

የወንጀሉ ዝርዝር

በአሁኑ አድራሻ ኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ቀበሌ 11 ልዩ ቦታው መስኪድ አካባቢ የሚኖረው ዘፀዓት ተወልደ ሐጎስ ሆን ብሎ ሰው ለመግደል አስቦ ጨካኝነቱን እና አደገኛነቱን በሚያሳይ መልኩ በጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 6 ሰዓት ተኩል ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ስላንድ ሆቴል አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የትዳር አጋሩ ከሆነችው ሉዋም ውበት ንጉሤ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት አንገቱን አንቃ በመያዝ ጠረጴዛ ላይ በነበረ ቢላዋ ልትወጋው ስትል አንገቷን ግጥም አድርጎ በመያዝ ቢላዋውን ከነጠቃት በኋላ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሕፃን ልጁ ባለበት ሟችን የግራ አንገቷን በቢላዋ በመቁረጥ ጥልቅ ቁስል እንዲፈጠር አድርጓል::

የመረጋጊያ ጊዜ እያለው ሰውን ለመግደል ፍፁም ፍቃደኛ በመሆን በቀኝ በኩል የአንገቷን አከርካሪ ቆርጧል:: እንዲሁም ደረቷ አካባቢም ወግቷታል:: በመጨረሻም የመኖሪያ ቤቱን ከውጪ በመዝጋት ህፃን ልጃቸውን ይዞ የተሰወረ ሲሆን፤ ሟች በደረሰባት አንገት ላይ የመቆረጥ እንዲሁም ደረት ላይ የመወጋት ጉዳት ምክንያት ሕይወቷ አልፏል:: በመሆኑም ተጠርጣሪው ዘፀዓት ተወልደ ሐጎስ በከባድ ሰው የመግደል ወንጀል ተከሷል ሲል የወንጀል ማስረጃው ያትታል::

ለክሱ በማስረጃነት ሰባት የሰው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲካል እና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በቁጥር ጳሀ8/2890 በታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም የሟችን የአስክሬን ምርመራ ውጤት ከእነ ትርጉሙ አቅርቧል::

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ በደብዳቤ ቁጥር ፌፎ /ባ-36/3099/2013 የተላከ ደብዳቤ እና የሟችን የአሟሟት ሁኔታ እና ጉዳቱን የሚያሳይ ማስረጃ፤ እንዲሁም 14 ፎቶ በተጨማሪ ግድያው የተፈፀመበት ቢላዋም በማስረጃነት ለፍርድ ቤት ቀርቧል::

ውሳኔ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት የ6 አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት ይቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ሆኖም ይግባኝ በመጠየቅ በድጋሚ ክርክር ከተካሔደ በኋላ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን የቅጣት ውሳኔ በመሻር የወንጀል ፈፃሚውን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል ብሎ ባመነበት በ15 ዓመት ፅኑ እስራት ይቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You