ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የሰጠችው ትኩረት በቀጣናው ተመራጭ መዳረሻ እያደረጋት ነው

አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የሰጠችው ትኩረት በቀጣናው የትብብር ማዕከልና ተመራጭ መዳረሻ እያደረጋት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ተናገሩ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የቻይና አፍሪካ (ኢትዮጵያ) የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ጉባኤ (ኮንፈረንስ) በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባቷን ተከትሎ የካፒታል ገበያ፣ የባንክ ኢንዱስትሪውና ሌሎችም አዳዲስ ዘርፎችም ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ተደርገዋል። እንዲሁም ለባለሀብቶች ምቹ የአሰራርና የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸው በቀጣናው የትብብር ማዕከልና ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን እያደረጋት ነው።

ኢትዮጵያ ባላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ፣ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብትና ሌሎችም ምክንያቶች ቻይና ትልቋ የኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞችን በማካሄድ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አሰራርን በመከተል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጥረት እያደረች ነው ብለዋል።

የጂያንግሱ ግዛት ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች 76 ኩባንያዎችን ከፍተው እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አህመድ፤ የቻይና ባለሀብቶች በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም በግብርናው፣ በማዕድን፣ በዲጂታልና በማምረቻው ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው፤ ይህ ጉባኤ ከኢትዮጵያ አልፎ መላው አፍሪካውያን ከቻይና ጋር ለሚያደርጉት የጠበቀ ግንኙነት መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸው፤ ቻይና ለኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎችም ዘርፎች ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት አምባሳደሩ፤ ቻይና ትልቋ የኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን ተናግረዋል።

ጉባኤው የሁለቱን ሀገራት እንዲሁም በቻይናና አፍሪካ መካከል ያለውን የምጣኔ ሀብትና የንግድ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ሀገራት በመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና አቅም ግንባታ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውና በቻይና ባለሀብቶች የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረምና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ያላት የምጣኔ ሀብት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጋለች። ቻይና ለአፍሪካ ልማት ለምታደርጋቸው ትብብሮችም ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ናት።

የጂያንግሱ ግዛት ዋና ገዥ ሹ ኩሊን የግዛቷን የምጣኔ ሀብትና ኢንቨስትመንት አቅም ባብራሩበት ወቅት ግዛቷ በቻይና በፈጣንና በሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ተጠቃሽ መሆኗን ገልጸው፤ በሰው ኃይል ልማት ላይ እየተሰራ ባለው ስራ 172 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማፍራት መቻሏን ጠቁመዋል።

ሚስተር ሹ ኩሊን እንደሚናገሩት፤ ባለፈው ዓመት በጂያንግሱ ግዛትና በኢትዮጵያ መካከል በወጪና ገቢ ንግድ ከ480 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተንቀሳቅሷል። ኢትዮጵያ የጂያንግሱ ግዛት ንግድና ኢንቨስትመንት ጠንካራ አጋር ስትሆን በአሁኑ ወቅትም የግዛቷ በርካታ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተዋል።

ጉባኤው በቀጣይም ከአፍሪካ ጋር በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪና ሌሎች የትብብር መስኮች ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር የሚያግዝ ነው ያሉት ሚስተር ሹ፤ ቻይና ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና ምጣኔ ሀብት ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክረው አመላክተዋል።

ሚስተር ሹ ጂያንግሱ፤ ግዛቷ ትልቅ የምጣኔ ሀብትና ኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት ገልጸው፤ በቀጣይም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ መሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የትብብር መስኮች ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር እንሰራለን ነው ያሉት።

በጉባኤው ላይ በኢትዮጵያ ስለሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የኢትዮጵያ የቢዝነስ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You