- የስደት ተመላሾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ:- ሕገ ወጥ (መደበኛ ያልሆነ) ስደት አሁንም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ መሆኑን በመገንዘብ በትኩረት ልንሠራ ይገባል ሲል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ለሶስት ዓመታት የስደት ተመላሾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ዙር ፕሮጀክት ትናንት ይፋ ሆኗል።
ፕሮጀክቱ የፍልሰት አስተዳደርን የበለጠ ለማጠናከር፣ ስደተኞችን ለመጠበቅ እና በኢትዮጵያ ያለውን መደበኛ ያልሆነ ስደት ለመቅረፍ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መደበኛ ሕገ ወጥ ስደት አሁንም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ ወጥ ስደትን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል።አሁንም በትኩረት ልንሠራ ይገባል።
ደህንነቱ የተጠበቀ፣ መደበኛ እና ክብር ያለው ስደት በሕገወጥ ስደት ወቅት የሚያጋጥሙ አደጋዎችን እንደሚያስቀር ገልጸው፤ኢትዮጵያና ኔዘርላንድ ሕገ ወጥ ስደትን ለመዋጋት አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዚህም ተመላሽ ስደተኞችን መልሶ ማቋቋምና ድጋፍ ማድረግ፣ በስደት አስተዳደር እና ጥበቃ ጉዳዮች ላይ የአቅም ማጎልበት ሥራዎችን በሚመለከት ከኔዘርላንድ መንግሥት ጋር በትብብር የተለያዩ ሥራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ክሪስቲን ፒሬን በበኩላቸው፤ ይህንን አጋርነት በማራዘም ኔዘርላንድ እና ኢትዮጵያ የስደትን ውስብስብ ችግሮች ለመቅረፍ ቀጣይነት ያለው ትብብር እንደሚኖራቸው አመልክተዋል።
እ.ኤ.አ. በ2021 የተጀመረው የፍልሰት ዘላቂ መፍትሔዎች ለማምጣት የሚደረግ ትብብርና አጋርነት ፕሮግራም ቀደም ሲል ስደተኞችን እና ከስደት ተመላሾችን በመደገፍ ረገድ ጉልህ እመርታ ማምጣቱን ተናግረዋል።
የስደት ተመላሾችን ተጠቃሚ በሚያደርገው በዚህ ፕሮጀክት ሕገ ወጥ ስደትን በመከላከል፣ በመልሶ ማቋቋም፣ በአቅም ግንባታ እና መደበኛ ባልሆነ የስደት አደጋዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም