ወጣትነት ሰፊ ጊዜ ፣ በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊነት፣ ብርቱ ጉልበት ብዙ ነገር መፍጠር የሚችል የነቃ አዕምሮ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ ስኬትንም ሆነ ውጤታማነትን በዚህ አጓጊ የእድሜ ወቅት ላይ ለማግኘት እነዚህን በረከቶች መረዳት ያስፈልጋል ፡፡ አብዝቶ መሞከር ፣ እድልን መጠቀም ፣ እንደ ብርቱ ጉልበት ሁሉ ተስፋ ለመቁረጥ በፍጹም ያልተዘጋጀ ደንዳና ልብ ይፈልጋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻ ከሁለት ‹‹ በከንፈርሽ በራፍ ›› የተሰኘ የራሱን ሶስተኛ የግጥም መጽሐፍ ለሕትመት ያበቃው ገጣሚ እና ፀሐፊ ዮሐንስ ሞላ በፌስቡክ የማህበራዊ ገጹ ያጋራው ጽሑፍ ነው ፡፡
ጽሑፉ አንድ በእጆቹ በርከት ያሉ መጻሕፍትን የያዘ ወጣት ፎቶ አያይዟል፡፡ የራሱን መጽሐፍ ግዙኝ እያለ እሱ በሚገኝበት የመዝናኛ ስፍራ አግኝቶት በማህበራዊ ገጹ ያሉ ሰዎች ጭምር እንዲገዙት የሚያትት እና የሚያበረታታ ነው፡፡ ወጣት ተመስገን ታደሰ ይባላል፡፡ በዛሬው የወጣቶች ገጻችን የራሱን መጽሐፍ እያዞረ እስከ መሸጥ ያደረሰውን አጋጣሚ እና የሕይወት ጉዞ እንዲህ አጋርቶናል፡፡
ትውልድና እድገቱ ምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ ውስጥ ጣዕመ በተባለ ትንሽ የቀበሌ መንደር ውስጥ ነው። ለወላጆቹ የመጨረሻ እና አስረኛ ልጅም ጭምር ነው። ሥነ-ጽሑፍ እና ተመስገን ትውውቃቸው ከልጅነት ጀምሮ ነው። ጥሩ የማንበብ ልማድ፣ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ክበቦች ላይ የነቃ ተሳትፎ ነበረው። ትምህርት ቤት የቀለም ትምህርትን መማሪያ ብቻም ሳይሆን ተማሪዎች ያላቸውን ዝንባሌ አውጥተው የሚሞክሩበት በአቅማቸው ራሳቸውን የሚፈልጉበት ሥፍራ ነው፡፡
ታዲያ ተመስገንም የልጅነት ጊዜው ለሚወደው ሥነ-ጽሑፍ እና ግጥም ቦታ የሰጠ ነበርና በተለያዩ ክበቦች ፣ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ የራሱን የግጥም ሥራዎች ያቀርባል፡፡ የተመስገን ወላጆች ልክ እንደ አብዛኛው ቤተሰብ ኪነ-ጥበብም ሆነ ሥነ-ጽሑፍ ልጆቻቸው እንዲገፋበት የሚፈልጉት ዘርፍ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በዚሁ ከቀጠለ እንዴት ራሱን ማስተዳደር ይችላል የሚል ስጋት ነበራቸው፡፡
ተማሪ ሳለ ህልሙ መሃንዲስ መሆን ነበር። ገጣሚ መሆንንም የሚተወው ጉዳይ አይደለም። ከልጅነቱ ጀምሮ ከሚያነባቸው ገጣሚያን እና ጸሐፍት መካከልም ገጣሚ እና ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ ወዳጅ ነው፡፡ ታዲያ በትምህርት ቤትም ሆነ በሚኖርበት ከተማ ውስጥ የሚዘጋጁ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ መድረኮችን እየተሳተፈ የመሰናዶ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት ጊዜው ደረሰ፡፡ የተመደበው እሱ ከሚኖርበት ስፍራ ርቆ የሚገኝ እና ፍጹም የተለያየ አየር ጸባይ ያለው አካባቢ ነበር፡፡
‹‹የተመደብኩበት አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ እኔ ያደግሁበት ቦታ ደጋ እና በጣም ቀዝቃዛ ነው። አሶሳ ደግሞ በጣም ሙቀት ነው፡፡›› የሚለው ተመስገን በዚያ የነበረው ቆይታ ለመልመድ አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶበት እንደነበር ይናገራል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ለመማር የመረጠው የትምህርት ዘርፍ የልጅነት ህልሙን ከግምት ያስገባ ነበር፡፡ የሲቪል ምህንድስና ትምህርትን ምርጫው አድርጎ ትምህርቱን መማር ቀጠለ፡፡ ለሥነ-ጽሑፍ ያለውን ዝንባሌም አልተወውም፡፡ ‹‹ተማሪ እያለሁ እንደምንቀሳቀሰው ባይሆንም በተለያዩ ክበቦች ላይ እና ጊቢ ውስጥ የሚዘጋጁ መድረኮች ላይ የግጥም ሥራዎቼን አቀርብ ነበር፡፡››
ተመስገን ሃሳቡን የሚገልጽበትን ግጥም በተለያዩ ደብተሮች ላይ በማስፈር እና በማከማቸት ለሌሎች ሰዎች የሚጋራበትን መንገድም ይፈለግ ነበር፡፡ ‹‹የምጽፋቸውን ግጥሞች አስቀምጥ ነበር እና በአንድ ወቅት ስመለከተው በጣም ብዙ ሆኖ አገኘሁት፤ ባሳትመው የሚል ሃሳብ መጣልኝ፡፡ ከዚያም ከግጥሞቼ ውስጥ መምረጥ እና ረቂቅ ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡›› ይላል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለው የባሕል እና ቱሪዝም ክፍል በተለያየ ወቅት ዝንባሌ ላላቸው ሰዓሊያን የፊልም ባለሙያዎችን የማገዝ ልምድ እንዳለው ተመስገን መረጃውን አገኘ፡፡ በመሆኑም የግጥም ሥራውን የሚያሳትምበትን አንዱን መንገድ ሞከረ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የባሕልና ቱሪዝም ክፍል የመጀመሪያ መጽሐፉን ለሕትመት ለማብቃት እንዲያግዙት ጥያቄውን አቀረበ፡፡ ጥያቄው ተቀባይነት አገኘ፡፡ ያቀረበው የግጥም ጽሑፍ ረቂቅም አልፎ ለሕትመት እንዲበቃ ፍቃድ ቢያገኝም አንድ ጉዳይ ግን ተመስገንን አልተስማማውም፡፡
‹‹መጽሐፉን እንዳሳትም ቢፈቅዱልኝም ግን መጽሐፉ ታትሞ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ብቻ እንዲሆን ነበር የፈቀዱት፡፡ እኔ ደግሞ እንደዛ እንዲሆን አልፈለኩም ነበር፡፡›› ሃሳባቸውን በብዕር በኩል ወረቀት ላይ አስፍረው ድርሰት ቢሆን አልያም ግጥም ከሃሳብ ሃሳብ ፤ ከእይታ የተለየ አተያይ እና ቃላት ተመርጦ ደራሲ ጋር ያለን ጽሑፍ ወደ አንባቢ መሳለፍ ለፀሐፊው ልጅን የመውለድ ያህል እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡
ተመስገንም የመጀመሪያ የሆነውን የግጥም መድብሉን ለማሳተም የጀመረው ሂደት ታትሞ እስከሚያየው ድረስ ልቡን ስቅል አድርጎት ነበር። በመሆኑም የራሱን መንገድ ተጠቅሞ መጽሐፉን ለሕትመት አበቃው፡፡ የመጀመሪያው የሆነው የግጥም መድብል እና የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2010 ዓ.ም ይዞ ተመረቀ፡፡
‹‹ለማሳተም በጣም ጓጉቼ ስለነበር ልመረቅ ስል ሱፍ ልገዛበት የነበረውን ገንዘብ አነስተኛ ኮፒ ያለው እትም አድርጌ አስመረቅሁት፡፡ ከመጽሐፌ ጋር አብረን ነው የተመረቅነው፡፡›› ሲል ሁኔታውን ያስታውሳል፡፡
የመጀመሪያ የግጥም መድብሉ ‹‹የጣዕመ ማህጸን›› የተሰኘ ሲሆን የምርቃት ሥነ-ሥርዓቱም በተማረበት ክፍል ውስጥ ከተማሪ ጓደኞቹ እና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ነበር፡፡ ጣዕመ ተመስገን ተወልዶ ያደገባት የመንደር ቀበሌ ስትሆን የተሰየመችውም ከተማውን በጃንሆይ አጼ ኃይለሥላሴ ወቅት ያስተዳድሩ የነበሩ ብዙ ሥራዎችን የሰሩ ነገር ግን ብዙ ያልተወራላቸው ደጃዝማች ጣዕመን ለመዘከር በማሰብ የተሰየመ ርዕስ ነው፡፡ ‹‹የታተመው ትንሽ ኮፒ ቢሆንም ግን በጊዜው ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ታዋቂ የሆኑ እንደ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ ያሉ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ተዋውቄበታለሁ፡፡›› ይላል፡፡
የተመስገን የመጀመሪያ ዲግሪ እና የመጀመሪያ የሆነው የመጽሐፍ ሥራው የጣዕመ ማህጸን አብረው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን ጨርሰው ወጡ፡፡ ተመስገን የቀረውን የመጽሐፍ እትም ይዞ ወደ ተወለደባት ከተማ በመሄድ ቀሪውን በዚያ ለሚገኙ ጓደኞቹ እና የተለያዩ የኪነጥበብ ማህበራት ላይ መጽሐፉን ለማስተዋወቅ ችሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ቆይታውን ካጠናቀቀ በኋላ ቀጣዩ ምዕራፍ ሥራ መፈለግ ነበር፡፡ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በሲቪል ምህንድስና በመሆኑ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር አንድ ለአምስት በመደራጀት ከመንግሥት የሚሰጣቸውን የተለያዩ የኮንስትራክሽን ሥራዎች በኮንትራት ተቀብለው ሰርቶ አጠናቅቆ የማስረከብ ሥራን ጀመሩ፡፡ በዚህ ሥራ የተመስገን ኃላፊነት ምንም እንኳን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ቢሆንም ነገር ግን ቆሞ ማዘዝን በፍጹም አይፈለግም፡፡ ‹‹እኛ ከሌሎች የግል ኮንትራክተሮች ጋር የመጫረት አቅም ስለሌለን መንግሥት ነው ፕሮጀክቱን እና የተቆረጠ መሥሪያ ገንዘቡ ይሰጠናል። ስለዚህ ሁላችንም እኩል እንሠራለን ፤ ሠራተኛ ቀጥረን የምናሠራው የማንችለውን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ኢንጂነር ሄልሜት ለብሰን የምናሰራ ከሆነ የምናተርፈው ገንዘብ አይኖረንም፡፡›› በማለት የነበራቸውን ሥራ ትጋት ያስታውሳል፡፡
ተመስገን የጀመረው አዲስ ሥራ ፕሮጀክት በመሆኑ አንድ ፕሮጀክት ሰርተው ካጠናቀቁ በኋላ ሌላ ፕሮጀክት እስኪሰጣቸው ድረስ ሰፊ የሆነ ጊዜን ያሳልፉ ነበር። በመሆኑም ይህንን ትርፍ ጊዜ ተመስገን ሌላ ተጨማሪ ትምህርት በርቀት መርሀ ግብር የአካውንቲንግ ትምህርትን በድጋሚ መማር ቀጠለ፡፡
ሕይወትን በተሻለ መንገድ ለመምራት የተለያዩ መንገዶችን የሚሞክረው ተመስገን በዚህ መሀል ተሰጥኦው የሆነውን የግጥም ሥራዎቹን እየጻፈ ማስቀመጡን እንዲሁ አልተወም፡፡ በኮንስትራክሽን ሥራው የሚያገኘውን ገቢ በማስቀመጥ እና በማጠራቀም ሁለተኛ መጽሐፉን ለማሳተም አገዘው። ‹‹50 በመቶ ለማሳተም የሚያግዘኝ ሰው አግኝቼ ነበር። ነገር ግን ለማሳተም ሕትመት ቤት ከተስማሙ በኋላ ሃሳባቸውን ቀየሩ፡፡›› በማለት ወቅቱን የሚያስታውሰው ተመስገን ሊያሳትም ከነበረው የእትም ብዛት በግማሽ በመቀነስ ሁለተኛ መጽሐፉ የሆነው ‹‹አለት ያጣ ንስር ›› የግጥም መድብል በ2014 ዓ.ም እንዲታተም አደረገ፡፡
‹‹ተወልጄ ባደግሁበት ከተማ የወጣት ማህበር አለን እና ማህበሩ በሚሰበሰብበት ወቅት ሌሎች የሚመጡ እንግዶች ባሉበት ተመርቋል፡፡›› ተመስገን እነዚህን ሁለት መጽሐፎች ሲያሳትም ራሱ አሳትሞ የሚገዙ ሰዎችም ካሉ የሚገዙት ከራሱ ከፀሐፊው እጅ ነበር፡፡ ‹‹አሳታሚዎች መጽሐፉን ተቀብለው መሸጥ ይፈልጋሉ ግን ቅድመ ክፍያ አይሰጡም፡፡ መጽሐፉ ከተሸጠ በኋላ ነው የሚከፍሉት። የግጥም መድብል ሲሆን ደግሞ ሰዎች አይገዙም የሚል ሃሳብ ስላላቸው ለመግዛት ፍቃደኛ አይደሉም፡፡›› ሲል መጽሐፍ ጽፎ ለመሸጥ ያለውን ውጣውረድ ይናገራል፡፡
ተመስገን የሕትመት ዋጋ መጨመር ፣ ከታተመ በኋላ ተቀብለው የሚሸጡ የመጽሐፍት መደብሮችን አለማግኘት ከባድ ፈተና እንደሆነ ተመስገን ይገልጻል።
የሁለተኛ መጽሐፍ እትም እንዳበቃ ተመስገን በርቀት ይማር የነበረውን ትምህርት አጠናቀቀ፡፡ ቀጣዩ ሃሳብም አዲስ አበባ የምትኖር እህቱ ጋር በመምጣት በዚህ የተማረው የአካውንቲንግ ትምህርት ሥራውን መፈለግ ጀመረ፡፡ ‹‹መጀመሪያ የተማርኩት ሲቪል ኢንጂነሪንግ ቢሆንም አሁን ላይ የምተዳደርበት ግን ሁለተኛ ላይ በተማርኩት ትምህርት ነው፡፡›› ተመስገን በመገረም የሚያነሳው ሃሳብ ነው፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ባገኘው የባንክ ሥራ ሕይወቱን መምራት ጀመረ፡፡ ነገር ግን የግጥም ሥራውን አልተወውም ነበር፡፡ በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች ላይ ግጥሞቹን ማንበብ እና የኪነጥበብ መድረኮች ላይ ሥራዎቹን ማቅረብ ጀመረ፡፡ ተመስገን ጽሑፍ ከልጅነቱ ጀምሮ የሚወደው በመሆኑ የሁለተኛ መጽሐፉን ሁለተኛ እትም በድጋሚ ለማሳተም አሰበ። ‹‹ ለሁለተኛ ጊዜ ለማሳተም የፈለኩበት ምክንያት የመጀመሪያው እትም የሚስተካከሉ እንከኖች ነበሩት። የተሸጠውም እኔ ባደግሁባት ከተማ ብቻ በመሆኑ ከብዙ ሰው ጋር አላስተዋወቀኝም ነበር፡፡››
የግጥም መጽሐፍን በራስ ወጪ ማሳተም እና ለገበያ ማውጣት ያለውን ፈተና ተመስገን አስቀድሞ የተረዳ ቢሆንም ነገር ግን ከመሞከር ወደኋላ ማለት እና ህልሙን መተውን አልፈቀደም፡፡
‹‹ለሁለተኛ እትም የሚሆነኝን ገንዘብ ከመሥሪያ ቤቴ የሶስት ወር ደሞዝ አስቀድሜ በመውሰድ ነበር ያሳተምኩት፡፡›› የሚለው ተመስገን መጽሐፉን ካሳተመ በኋላ ራሱ ለተለያዩ የመጽሐፍ መደብሮች ያከፋፍል ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በርካታ የሚባል መጽሐፍ በቤቱ ውስጥ ተቀመጠ። ተመስገን በዚህን ጊዜ ነበር ለምን ራሴ እያዞርኩ አልሸጠውም የሚል ሃሳብ የመጣለት፡፡
ታዲያ የራስን መጽሐፍ እያዞሩ መሸጥ አይከብድም ወይ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ‹‹የራስን መጽሐፍ አዙሮ መሸጥ ማለት አንድ ገበሬ ዘርቶ የሰበሰበውን እህል ራሱ ወደ ገበያ ወስዶ አልያም እያዞረ ሲሸጠው እንደ ማለት ነው፡፡ የሰው ፊት መቆም ከባድ ሊመስል ይችላል። ግን ፍርሃቱ የሚኖረው ከአንድ እና ሁለት ደቂቃ ያላነሰ ነው፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ተመስገን መጽሐፉን እንማንኛውም የመጽሐፍ አዟሪ መጽሐፉን ለመሸጥ ወሰነ፡፡ በተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች በማምራት ኃላፊዎችን የራሱ መጽሐፍ እንደሆነ በመናገርና በማስፈቀድ በቦታው ላሉ ሰዎች ራሱን እያስተዋወቀ መሸጡን ቀጠለ፡፡ አንዳንዴም ከሥራ ቦታው ወደቤቱ በሚሄድበት ጊዜ እግረ መንገዱን በሚያገኛቸው ሆቴሎች ገብቶ ይሸጣል፡፡ ‹‹መጽሐፍ አዟሪዎች ሲያገኙን በሥራዬ ገባህ ይሉኛል፡፡ የራሴን መጽሐፍ ግዛኝ ያለኝ ሰውም አጋጥሞኛል፡፡›› ይላል፡፡
ተመስገን መጽሐፍን በራሱ የመሸጥ ሥራውን የእረፍት ጊዜውን በመጠቀም የራሱን መጽሐፍ በ10 ወር ጊዜ ውስጥ 800 የሚደርስ መጽሐፍን አዙሮ ሸጧል፡፡ ‹‹በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰው ቢዚ ነው ገንዘብ ማውጣት አይፈለግም፤ አንዳንዱ ደግሞ ከንፈር የሚመጥም አለ፡፡›› ሲል የሁኔታውን አስከፊነት ያስረዳል፡፡
በዚህ ወቅት ልክ እንደሱ ገጣሚ የሆኑ የኪነ ጥበብ ሰዎችን የራሱ መጽሐፍ እንደሆነ ሲነግራቸው በጣም ያዝናሉ፡፡ ተመስገንም የራሱ መተዳደሪያ ሥራ እንዳለው ይነግራቸዋል፡፡ ከእነዚህ ገጣሚያንም ሆኑ ደራሲያን የእርሱን መጽሐፍ ገዝተው ለማበረታታት የራሳቸውን መጽሐፍ በስጦታ እንደሚበረክቱለትም ያስታውሳል፡፡
ተመስገን የመጣበት መንገድ እና ህልሙን ለማሳካት የተጓዘባቸውን መንገዶች እንደ ጥሩ እድል እንጂ እንደ መጥፎ አጋጣሚ አይቆጥራቸውም፡፡ ምክንያቱም በወሰነው ውሳኔ የሚፈልገውን ህልሙን ለማሳካት እና አንድ ርምጃ መራመድ ችሏል፡፡ ለሌሎች ወጣቶችም ህልማቸውን ለማሳካት የሚያግዳቸውንም ከሰዎች የሚሰጣቸውን አስተያየት መፍራት እንደማይገባ ይገልጻል፡፡
ተመስገን አሁን የሚገኝበት የባንክ ሥራ ውስጥ አንድ ዓመት ያህል ጊዜን አስቆጥሯል፡፡ በቀጣይ በዚሁ ሥራ ላይ በመቀጠል በጎን ደግሞ ጥሩ ጥሩ መጽሐፎችን በመጻፍ ሰዎች ፈልገው ገዝተው የሚያነቧቸውን ተወዳጅ የመጽሐፍ ሥራዎች ማሳተም ህልሙ ነው፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም