አዲስ አበባ– ቱሪዝም ሚኒስቴርና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ያደረጉት ስምምነት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ወደ ኢኮኖሚ መለወጥ የሚያስችል ብቁ አመራር መፍጠር እንደሚያስችል የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ቱሪዝም ሚኒስቴርና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ብቁ አመራሮችን ለመፍጠር የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ ትናንት ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ ወቅት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ እንደገለጹት፣ እንደሀገር ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ የዕድገት ምንጭ ተብለው ከተለዩት ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንደኛው ነው፡፡ በሂደቱ በመንግሥት በኩል ፖሊሲ ተነድፎ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ለዘርፉ ኢንቨስትመንትም በርካታ ድጋፎች እየተደረጉ ነው፡፡ ይህ ከሀገር ውስጥ ባሻገር በቀጣናውና በአህጉር ደረጃ መታየት የሚችሉ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት የአቅም ማሳደግ ሥራ መሥራት ወሳኝ ነው። ስምምነቱም ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብት ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን ሀብቱን ወደ ኢኮኖሚ መለወጥ የሚያስችል ብቁ አመራር መፍጠር እና በዘርፉ ያለውን ስብራት በመጠገን ወደ ውጤት ለመቀየር ያለመ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ፤ በንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢጋድ የቱሪዝም ሻምፒዮን ሆነው መመረጣቸው አስታውሰው፤ በአፍሪካ ህብረት ጭምር ኢትዮጵያ ያላት ዕምቅ የቱሪዝም አቅም እውቅና ተሰጥቷታል፡፡ የብሪከስ አባል መሆኗ ከሀገራት ጋር በጋራ የሚሠራበት የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአባል ሀገራቱ ያለው የቱሪዝም አቅም መጠቀም የሚቻልበትን እና በሀገራቱ መካከል የአመራር አቅም ማሳደግ አብሮ የሚሄድ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ የሚፈለገውን ዕድገት ማምጣት እንዲችል እና በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ከፍ ማድረግ የሚቻለው በዘርፉ ውስጥ ያለው መዋቅራዊ ስብራት ማከም ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ በተለያዩ የሙያ መስክ ያሉ አካላትን በአመራር የአቅም የማሳደግ፤ የማላቅ ብቁ አመራሮችን የመፍጠሩ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶተታል ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉ ከመንግሥት ባሻገር የግል ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ ያለበት መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ በዘርፉ ያለው አመራር አቅም ማሻሻል አስፈላጊና ብቁ አመራሮችን ለመፍጠር ስምምቱ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው አንድ ተቋም ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ መዋቅራዊ ትስስር (ecosystem integration ) ያስፈልጋል፡፡ አንድ ተቋም ብቁ አመራር ፈጥሯል የሚባለው መዋቅራዊ ትስስሩ አመራር መፍጠር የሚችል የፖሊሲ ግልጽነት፤ የአመራር ልማት ፕሮግራም ሲኖር፤ የአመራር ብቃት መለኪያ፤ የአመራር ልቀትና እና በተቋም ላይ የመተግበር ብቃት መሠረት ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አንድ አመራር ውጤታማ የሚሆነው ግልጽ የሆነ የፖሊሲ ሲኖር ነው። አካዳሚው ቀጣይነት ያለው የአመራር ልማት ፕሮግራም ላይ እየሠራ ነው። ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነት ፖሊሲውን የተረዳ ብቁ አመራር ለመፍጠር ነው። በሁለቱ ተቋማት ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ለሀገራዊ ዕድገት እንዲውል ማድረግና ጠቅላላ አመራር ልማት ፕሮግራም እና የቱሪዝም ዘርፍ ልዩ አመራር ልማት ፕሮግራም ሥርዓተ ሥልጠና (ካሪኩለም) ቀረጻ ሥራዎችን በጋራ መሥራት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም