ቅርስ ማስመለስ ሌላኛው ኢኮኖሚ ገጽታ

በጥቅምት ወር 2017 እኤአ 1868 በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተወሰደው የአጼ ቴዎድሮስ ጋሻ ከ156 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ማስመለስ ተችሏል።በሳለፍነው ታህሳስ ወር 2016 ዓመተ ምህረትም የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ፀጉር፣ ሁለት በብር የተለበጡ ዋንጫዎች፣ አንድ የቀንድ ዋንጫ፣ ደብዳቤዎች እንዲሁም አንድ ጋሻ ተመልሷል።

በተጨማሪም የጥቁር ሁሉ ድል በሆነው ዓድዋ ጦርነት ወቅት አገልግሎት ላይ ውሎ የነበረው የዳግማዊ ምኒልክ ጎራዴ፣ የእንጨት መስቀልና ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተላላኳቸው ደብዳቤዎች፣ ፎቶግራፎች፣ የፅሁፍና የምስል ቅርሶች ወደ እናት ሀገራቸው ተመላሽ ሆነዋል።ታዲያ እነዚህ ቅርሶች ከማንነት መገለጫ ከትውልድ መማሪያነት በዘለለ ሌላኛው የኢኮኖሚ ዋልታ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ይላሉ የዘርፉ ምሁራን።

ሀገራች ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች ውስጥ አንዱ አድርጋ መሥራት ከጀመረች ውላ አድራለች። የተለያዩ አዳዲስና ታሪካዊ ቦታዎችን በዘመናዊ መልኩ የቱሪስት መዳረሻ አድርጋ ማልማት መጀመሯም ለዚሁ ማሳያ ነው።

የከተሞች የኮሪደር ልማት እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርምም የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር በዘርፉ ያለው ተጠቃሚነት ያጎለብታል።ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎንም በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር የወጡ ቅርሶች ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ደግሞ ቱሪዝሙ ለኢኮኖሚው ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ ሌላኛው ገጽታ መሆኑን ይናገራሉ።

በእርግጥ ቱሪዝሞ መልኩ ብዙ ነው።ሰፊና የተለያዩ ዘርፎች የያዘ።ከእነዚህም ዘርፎች ውስጥ ቅርስ አንዱ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት የተዘረፉ ቅርሶች መመለሳቸው ለሀገር ኢኮኖሚው ምን አይነት አንደምታ አለው ሲል ኢፕድ የዘርፉ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

የቱሪዝም ባለሙያ መምህርና ተመራማሪ አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚሉት ቅርሶች ለአንድ ሀገር የማንነትና የአንድነት መገለጫ ከመሆናቸው በላይ የቱሪስት መስህብ በመሆን የኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ነው።

ቅርሶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ አሏቸው የሚሉት ዶክተር አያሌው፣ ለተለያዩ ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ለመዝናኛነት የውጭ ምንዛሪ ለማስግኘት እንዲሁም የሀገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰቱ ለማሳደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

አሁን ላይ የተዘረፉ ቅርሶች ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም ውጤታማ ሥራ ለመሥራት በኢንተር ፖል አማካይነት ፣የተለያዩ ድርድሮች በማድረግና ተጽዕኖ በመፍጠር እንዲሁም የተለያዩ የማሳመን ችሎታ ያላቸው አካላት በማካተት በቅንጅት መሥራቱ አዋጭ እንደሆነ ያክላሉ።

ቅርሶች ለትውልድ የሚያጋጥሙት ተግዳሮት፣ ጥንካሬና ድክመቶች የሚያሳዩ በመሆናቸው ለመማሪያነት መጠቀም ያስፈልጋልም ነው የሚሉት።

ዶክተር አያሌው፤ ኢትዮጵያ አሁንም ያልተመለሱ በርካታ ቅርሶች እንዳሏት ጠቅሰው የብራና መጽሐፍት፣ መስቀሎች እንዲሁም የነገሥታት መጠቀሚያ ቁሳቁሶች በይበልጥ በምዕራባያውያን ሙዚየሞች ውስጥ እንደሚገኙ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ያብራራሉ።

በተለይ ቅርሶች በተናጠል ለማስመለስ ከመጣር ይልቅ በጋራ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ቢሠራ የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።

በጦርነት ከተወሰዱት ውጪ ጥንቃቄ ባለማድረግና የሀገር ኃላፊነት በማይሰማቸው ዜጎች በሽያጭ የተወሰዱ ቅርሶች አሉ የሚሉት ዶክተር አያሌው፣ የተዘረፉ ቅርሶች ከማስመለስ ጎን ለጎንም ቅርሶች ከሀገር እንዳይወጡ ጥንቃቄ ማድረግና በሚገባው ልክ ተጠቃሚ ለመሆን ድጋፍን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባለሉ።

የቱሪዝም ባለሙያና ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ፤ ቅርሶች ለቱሪዝም ፍሰት፣ ለመስህብነት፣ የማንነት መገለጫ እንዲሁም የኢኮኖሚ ምንጭነታቸው በተጨማሪ በራሳቸው ሀብት፣ ንብረት እውቀትና ጥበብ መሆናቸውን ይገልጻል።

ቅርሶች ለትውልድ መማሪያ በመሆናቸው ቅርስ ሲመለስ ከቅርሱ ጋር አብሮ የተዘረፈው ጥበብና እውቀት እንደመመለስ እንደሆነ ይቆጠራል።

እንደ ጋዜጠኛ ሄኖክ ገለጻ፤ ቅርሶች ኢኮኖሚውን ከማነቃቃትና ከመደገፍ አኳያ ለባለቤታቸው ሲመለሱ የሚስቡት ዓለም አቀፍ ትኩረትና የሚዲያ ሽፋን የቱሪስት መጠን ከፍ የሚያደርግ ነው።ይህም ቀጥተኛ በሆነ ሁኔታ ኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽጾ ይኖረዋል።

በተጨማሪም ከቅርሶች ጋር ተያይዞ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለማከናወን የሚወጡ ወጪዎች ለመቀነስ እንዲሁም የሌሎች ሀገራት ተመራማሪዎች ቅርሶቹን ለምርምር ሲፈልጉ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ።

በውጭ የሚገኙት ግለሰቦችና ድርጅቶች ቅርሶቹን ለማስመለስ ከመሟገት በላይ ገዝቶ እስከ መላክ መስዋዕትነት እየከፈሉ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል የሚለው ጋዜጠኛ ሄኖክ፣ ቅርስ በማስመለሱ ሂደት ሁሉም ዜጋ መረባረብ አለበት ይላል።

ጋዜጠኛ ሄኖክ፤ በተለያዩ ጊዜያት ለማስመለስ ከጥቂት ግለሰበቦችና ወዳጅ ሀገራት ውጪ በቅንጅት እየተሠራ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ በእንግሊዝ እንዳለው ኤምባሲ ሁሉም ኤምባሲዎች ጥረት ማድረግ በተለይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሂደቱ መሳተፍ አለባቸው ነው ያሉት።

መንግሥት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው በተለያዩ ሀገራት ሙዚየም የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚያደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላልም ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ናቸው።

የት ሀገር ምን ይገኛል የሚለውን ጥናት እየተደረገ መሆኑን እና በሕግ አግባብ የሚመለሰውን በሕግ በዲፕሎማሲ ጥረት የሚመለሰው በዲፕሎማሲ ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የሚናገሩት።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You