የቡና ጥራትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፡- አርሶ አደሩ ዘመናዊ የቡና ምርት ማዘጋጃ አሠራርና መሣሪያዎችን በመጠቀም የምርት ጥራትን እንዲያሳድግ የተጠናከረ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ገለፀ፡፡

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የቡና ልማት እና ጥራት ዳይሬክቶሬት አቶ ታከለ ኃይለማሪያም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ መንግሥት የቡና ምርትና ጥራትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከፍ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።

ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ለአርሶ አደሩ የቡና ምርት ማዘጋጃ ዘመናዊ አሠራሮችን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ዘመናዊ መሣሪያዎች በስፋት እየቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ቡና ለማምረት የሚጠቀምበት ባህላዊ መሣሪያዎችና አሠራሮችን የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተው፤ ቡና ለመጎንደል እና ለመቁረጥ የሚፈጀውን ጉልበትና ጊዜ ለመቆጠብ በርዳታ የተገኙት ዘመናዊ የመጎንደያና የጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽኖች ለአርሶ አደሩ እንዲከፋፈል መደረጉን ተናግረዋል።

ለረጅም ዓመታት ምርት የሰጡ የቡና ዛፎች በማርጀታቸው ምርትና ጥራት ላይ ችግር መፍጠሩን አስታውሰው፤ ችግሩን ለመቀነስ አዳዲስ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

በተጨማሪ የምርት ማበልፀጊያ መሣሪያዎች በመንግሥት በኩል ለአርሶ አደሩ እንዲዳረስ መደረጉ የቡና ምርት እና ጥራት እንዲጨምር ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ከሚመረተው ቡና አብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደሚዘጋጅ የገለፁት አቶ ታከለ፤ በክልሉ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሔክታር መሬት ላይ ቡና እየለማ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ የቡና ልማት ምርታማነቱ በሔክታር ከስድስት ነጥብ አምስት ኩንታል ወደ ዘጠኝ ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አመልክተው፤ ተጨማሪ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም የቡና ምርት እና ወደ ውጭ የመላክ አቅም እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

የቡና ምርት ጥራትና ለመጨመር የሚሠሩ ሥራዎች ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ከፍ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም አምራቾች በቀጥታ ለውጭ ገበያ ቡናን እንዲያቀርቡ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ አቶ ታከለ ገለፃ፤ አምራቹ ራሱ ወደ ውጭ ሲልክ በገበያ እና በአምራቹ መካከል ያሉት ደላሎች ይቀንሳሉ። በሥራ ላይ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ የቁጥጥር አሠራር በመዘርጋቱ ለውጦች እየታዩ ይገኛል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም

Recommended For You