በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጽናት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ስምምነት ተደረገ

አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያደረጉት ስምምነት በሀገሪቱ ዴሞክራሲን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት አንድ ርምጃ ወደፊት ለማራመድ የሚያስችል መሆኑን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ አስታወቀ፡፡

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት በትናንትናው እለት ተፈራርመዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር በመፍጠር በሀገሪቱ ዴሞክራሲን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት አንድ ርምጃ ወደፊት ለማራመድ ያስችላል፡፡

ሀገራቱ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት በኩል እያደረገች ያለውን ልምምድ እንዲሳካ እና ችግሮችን በመቅረፍ ወደፊት የምትራመድ ሀገር ለመገንባት የአመራር ልማት ሥራ አስፈልጊ መሆኑን አንስተው፤ የአመራር ብቃት ሥራ ከተሠራ የሚሳካና ስምምነቱም ጠንካራ የፖለቲካ ፖርቲ አመራር በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም በአካል ተቀራርበው የማያውቁና ከሩቁ እንደ ባላንጣ ይተያዩ የነበሩ ከተፎካካሪና ከገዢ ፓርቲ አመራሮች በጋራ የአንድ አመራር ልማት ፕሮግራም ሥልጠና የሚወስዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሚያሣልፉት የሥልጠና ጊዜያትም የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እርስ በዕርስ እንዲተዋወቁ በማድረግ ከፍተኛ የባህል ሽግግር ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የአመራር ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በሚፈጠረው የባህል ሽግግርም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር ብቃት የአንድ ሀገር የህልውና ጉዳይ መሆኑን አቶ ዛዲግ አንስተው፤ በዚህም ብቁ አመራር በመፍጠር በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ እና ለባህል ለውጥ መልካም እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በጋራ ምክር ቤቱ በዋነኝነት የያዘውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዓላማና በሀገሪቱ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ኋላቀር የፖለቲካ ባህል በመቀየር ዘመናዊና ጊዜውን የሚመጥን የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ዓላማ በመያዝ በሀገሪቱ ከ60 በላይ የሚሆኑ ሀገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎችን ይዞ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በስምምነቱም የጋራ ምክር ቤት አባላቶቹች የአቅም ግንባታ ትምህርቶችና ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ለማድረግ፣ የተለያዩ የምክክር መድረኮችንና ሰነዶችን ለማዘጋጀት እንዲሁም ጥናትና ምርምር በማካሄድ የጋራ ምክር ቤቱ የያዛቸውን ዓላማዎች የማሳካት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም

Recommended For You