ስምምነቱ የመዲናዋን ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚረዳውን መተግበሪያ ለማልማት ከአራት ተቋማት ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱ በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ መካከል ተፈርሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የስምምነቱ ዋና ዓላማ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኤጀንሲው ሲጠቀመው የነበረበት መተግበሪያ (ሶፍት ዌር) ማሻሻል ነው። ይህም ነዋሪዎች ፈጣን የዲጂታል አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

አዲስ አበባን ስማርት ከተማ ለማድረግ ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም ኦንላይን የአሠራር ሥርዓት እንዲኖር በማስቻል ቀልጣፋና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት ታቅዷል ያሉት አቶ ዮናስ፤ ይህም ሕገወጥ ተግባራትን ለመቅረፍ እና የመዲናዋን ነዋሪዎች በቁጥር ለመለየት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የመተግበሪያውን ደህንነት፣ ተደራሽነት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ከሳይበር ደህንነት አንፃር ይፈትሻል። በዚህም የሀገር ውስጥ አቅምን በማሳደግ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እውን ለማድረግ እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ናቸው።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እና የሥራ ውጤታማነት ላይ ማማከሩን ኢንስቲትዩት እንደሚሠራ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አማረ በበኩላቸው፤ በመዲናዋ የሚሰጡ አብዛኛው አገልግሎቶች ከሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ናቸው። በተለይ ከፋይናንስ አገልግሎቶች ጋር ያለውን የዲጂታል ትስስር ለማጠናከር የመሠረተ ልማትና የሶፍት ዌር ማሻሻያ ማድረግ አስፈልጓል። ለዚህም ሀገር በቀር አልሚ ድርጅት ይመረጣል ነው ያሉት።

ዲጂታል መታወቂያ ቅንጅታዊ አሠራር እንዲጠናከር ያደርጋል። ይህም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩል ሚና ይጫወታል ያሉት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርአያ ሥላሴ፤ ስምምነቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።

በተለይ የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህም የሀገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ገልጸዋል።

በመዲናዋ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ማሻሻያ ላይ ኢንሳ እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የማማከር ሥራውን የሚያከናውኑ ሲሆን ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ደግሞ የፋይዳ መታወቂያ አቅምን ያሳድጋል። ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እውን የማድረግ ጉዞ አካል መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You