ተኪ የኬሚካል ምርት ለኢንዱስትሪው ዕመርታ

በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች 48 ነጥብ ሁለት አልሙኒየም ስልፌት፤ 22 ነጥብ አራት ስልፈሪክ አሲድና አምስት ነጥብ አንድ ሀይድሮጅን ፐር ኦክሳይድ እንደሚጠቀሙ በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም አምራች ኢንዱስትሪዎች 81 በመቶ የሚሆነውን የኬሚካል ምርት የሚያገኙት ከሀገር ውስጥ የኬሚካል አምራች ፋብሪካዎች ሲሆን ሶስት በመቶ የሚሆናቸውን ከውጭ የሚገቡት ምርቶችን ይጠቀማሉ፤ 16 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ከሀገር ውስጥም የሚመረቱና ከውጭም የሚገቡ የኬሚካል ግብዓቶችን እንደሚጠቀሙ ጥናት ይጠቁማል፡፡

አምራቾች ከውጭ ተመርቶ የሚመጣ የኬሚካል ግብዓት የሚጠቀሙበት ምክንያት 51 ነጥብ አንድ በመቶ ከሀገር ወስጥ የተሻለ የዋጋ ቅናሽ ያለው በመሆኑ አመልክተው፤ የሀገር ውስጥ አምራቾች 22 በመቶ በተፈለገው መጠን ያህል ምርት ፤ 15 በመቶ የጥራት ችግር ስላለባቸው፤ 10 ነጥብ ሶስት በመቶ የሚሆኑት ሀገር ውስጥ መመረቱን አለማወቃቸው መሆኑን ጥናቱ ያብራራል፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ የኬሚካል ምርቶችን በተኪ ምርቶች በመተካት የኢንዱስትሪ፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ግብዓት በማሟላት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራች መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡ ከውጭ የሚገባን የተለያየ የኬሚካል ግብዓትን በሀገር ውስጥ በማምርት ኢንዱስትሪዎች የኬሚካል ምርት በቀላሉ እንዲያገኙና በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናውነ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

በሀገር ውስጥ ሶስት አይነት የኬሚካል ግብዓቶች እየተመረቱ ነው፤ ቀሪ የኬሚካል ምርቶችን ለማምረት የፋብሪካዎችን ማሽኖች የማደስና የመቀየር፤ በቴክኖሎጂን የማስደገፍ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች ያብራራሉ፡፡

የኬሚካሎች ግብዓቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የተራዘመ የትራንስፖርት ሂደት እንደሚያጋጥም፤፡ የተራዘመ የትራንስፖርት ሂደት መኖሩም የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዲያልፍ ወይም ለማለፍ እንዲቃረብ ምክንያት መሆኑ ይነሳል፤ ይህም በኢንዱስትሪዎች፤ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ይህና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚል ንቅናቄ በመፍጠር እየሠራች ትገኛለች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል፡፡

የአዋሽ መልካሳ የኬሚካል ፋብሪካ የምርት ጥራቱንና የማምርት አቅሙን ለማሳደግ የኬሚካል ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ምርምርና ልማት ማዕከል ባስጠናው ጥናት የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በብዛት ሶስት አይነት የኬሚካል አይነቶችን ማለትም አልሙኒየም ሰልፌት፤ ሰልፈሪክ አሲድና ሃይድሮጂን ፐር ኦክሳይድንን እንደሚጠቀሙ ይዳስሳል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኬሚካል ክላስተር ዳይሬክተር ወይዘሮ አስማ ረዲን ለኢፕድ እንዳብራሩት፤ የማኑፋክቸሪግ፤ የኢንዱስትሪ በአጠቃላይ አምራች ዘርፉ የኬሚካል ግብዓት ተጠቃሚ ነው፤ የአምራች ዘርፉን ለማሳደግ የኬሚካል ግብዓትን ሙሉ ለሙሉ በሀገረ ውስጥ የመሸፈን እየተሠራ ነው፡፡ ኬሚካሎችም በሀገር ውስጥ መመረታቸው ተጠቃሜዎች በቅርበት ምርቶችን እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲከሰት ከማድረጋቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት ሂደታቸው የተራዘመ ነው፤ የትራንስፖርት ሂደታቸው የተራዘመ መሆኑም አገልግሎት ጊዜያቸው የሚያልፍበት አልያም አጭር ጊዜ የሚሆንበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ይህም በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈጥረው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ኬሚካሎች በሀገር ውስጥ መመረታቸው ኢንዱስትሪዎች ከስር ከስር እየተጠቀሙ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ያደርጋል፤ ኬሚካሎችን በጥራት ለማምርት በትኩረት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

በአዋሽ መልካሳ የኬሚካል ፋብሪካ ሶስት አይነት የኬሚካል ግብዓት የማምረት ሥራ እየተከናወነ ነው፤ እየተመረቱ ያሉ የኬሚካል ግብዓቶችም ለኢንዱስትሪዎች ቀላል የማይባል ሚና እየተጫወቱ ነው፤ ተጨማሪ ኬሚካሎችን ለማምረት የትራንስፎርሜሽ ፕሮግራም ተቀርፆ እየተሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የአዋሽ መልካሳ የኬሚካል ፋብሪካ ማምረት ከጀመረ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል፤ ፋብሪካ ያለውን አቅም ተጠቅሞ የኬሚካል ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የአረጁ ማሽኖችን የማደስ፣ በቴክኖሎጂ የማስደገፍ፤ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ የማድረግ ተግባር እያከናወነ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

የሀገር ውስጥ የኬሚካል ግብዓት በማምርት ላይ የተሠማሩ ፋብሪካዎችን ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙና የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡ የኬሚካል አምራች ፋብሪካዎች በቴክኖሎጂ መደገፋቸውም ጥራት ያለው ምርት አምርተው የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት አልፈው ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ያደርጋቸዋል ሲሉ ይናገራሉ። ይህም የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ የራሱ ድርሻ አለው ባይ ናቸው፡፡

ለኢንዱስትሪዎች የተለያዩ የኬሚካል ግብዓት የሚያቀርቡ ኬሚካል አምራች ፋብሪካዎች ወደ ላቀ ትርንስፎርሜሽን እንዲሻገሩ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን የመሳብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሐድጉ ኃይለኪሮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኬሚካል ግብዓት ለኢንዱስትሪ፤ ለማኑፋክቸሪንግ፤ ለግብርናው በአጠቃላይ ለሁሉም አምራች ዘርፍ እድገት ወሳኝ ነው፤ ለሁሉም አምራች ዘርፍ ወሳኝ የሆነውን የኬሚካል ምርት በሀገር ውስጥ የማምረት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪዎች የኬሚካል ግብዓት በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንዲቻል የሀገር ውስጥ የኬሚካል ፋብሪካዎችን የማምረት አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ፡፡

አብዛኛው የሀገር ውስጥ የሚገኙ የኬሚካል ፋብሪካዎች እያመረቱት ያለው ግብዓት ካላቸው አቅም በታች ነው፡፡ የኬሚካል አምራች ፋብሪካዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲያመርቱና ከውጭ የሚገባን የኬሚካል ግብዓት በሀገር ውስጥ መተካት እንዲችሉ የቴክኒካል ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡

የሀገር ውስጥ የኬሚካል ፋብሪካዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲያመርቱ ያለባቸውን ማነቆ በየወሩ በጥናት የመለየት፤ ለችግሩ መፍትሔ የመስጠት፤ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ የማድረግና የማምረት አቅማቸውን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነውም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ያላቸውን የማምረት አቅም ተጠቅመው የሀገር ውስጥ ፍላጎትን እንዲያሟሉ፤ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ የሚያደርግ ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡

የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪው በብዛት ሶስት አይነት የኬሚካል አይነቶችን ማለትም አልሙኒየም ሰልፌት፤ ሰልፈሪክ አሲድና ሀይድሮጂን ፐር ኦክሳይድንን ይጠቀማል ሲሉ ጥናቱን ያቀርቡት የኬሚካል ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ምርምርና ልማት የገበያ ምርምር ልማት ዴስክ ሃላፊ አቶ አሉላ በቀለ አመልክተው፤ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች 48 ነጥብ ሁለት በመቶ አልሙኒየም ስልፌት፤ 22 ነጥብ አራት በመቶ ስልፈሪክ አሲድ ፣ አምስት ነጥብ አንድ በመቶ ሀይድሮጅን ፐር ኦክሳይድ እየተጠቀሙ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች 81 በመቶ የሚሆነውን የኬሚካል ምርት የሚያገኙት ከሀገር ውስጥ የኬሚካል አምራች ፋብሪካዎች ነው፤ ሶስት በመቶ የሚሆናቸውን ከውጭ ይጠቀማሉ፤ 16 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ከሀገር ውስጥም ከውጭም እየተጠቀሙ ነው ሲሉ በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ኬሜካሎችን ሀገር ውስጥ ለማምረት የፋብሪካዎቹን አቅም ለመገንባት የተሰጠው ትኩረት ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ይሆናል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You