አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለኢኮኖሚው እድገት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል

አዳማ:- አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ዙሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የገለጻና ውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ትናንት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።

አዲሱ ፖሊሲ የቀድሞ ፖሊሲ ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ሆኖም የቀድሞው ፖሊሲ የግብርና ምርቶችን አቅርቦትን ማሳደግና ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ክፍተት ነበረበት ብለዋል።

የግብርናና ገጠር ልማት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ፣ በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ ያሉትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ፖሊሲውን መከለስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የግብርናን ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ፣ የገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት በዋናነትም ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አብራርተዋል። ፖሊሲው ሀገሪቷ የምትከተለውን የብዝሃ-ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ለማሳካት የሚያግዝ ነውም ብለዋል።

ፖሊሲውን የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራው በቀጣይ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እስከ ዞን እና ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየመራ ያለውን ግብርና በሚመጥን ፖሊሲ ፣ አደረጃጀትና አመራር መደገፍ ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ እንደ ሀገር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ታስቦ የሚሰራው ሥራ ስኬታማ አይሆንም ብለዋል።

አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የተከለሰበት ዋነኛው ምክንያት አሁን ሀገሪቱ ካለችበት እድገት አንፃር በቂና አስቻይ ባለመሆኑ ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ በዚህም ወቅቱን የሚመጥን ፖሊሲ ማፅደቅ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩ ከግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ጋር በመሆን የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You