
ክፍል ሁለት
ባለፈው ሳምንት፤ በተለይም በንጉሳዊ ሥርዓቱ ዘመን አዝማሪ በፖለቲካ ውስጥ የነበረውን ሚና ጥናት ዋቢ አድርገን አይተናል። የዛሬው ጽሑፍም የዚያው ቀጣይ ክፍል ነው። የባለፈው ሳምንት በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስና በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥታት ላይ ያተኩር ነበር። የዛሬው ደግሞ በደርግ እና በኢህአዴግ ዘመናት ላይ ያተኩራል።
በደርግ ዘመነ መንግሥት፤ የማህበራዊ ፍትሕ እጦትን ለመግለጽ በአዝማሪዎች እንዲህ ተብሎ ነበር።
ውስኪም ይንቆርቆር ጮማውም ይቆረጥ
ፍቅርዬ እኔና አንቺ ሽሮ እንቆራረጥ
ዮሜሳን ለሆዴ ማን ይገዛልኛል
እንቆቆ እየጋቱ ‹‹ዶሮ ማታ›› ይሉኛል
በስምንተኛው ሺ ሲመሽ ተወልጄ
ጅቡን ጋሼ እላለሁ ተኩላውን ወዳጄ!
በደርግ ዘመነ መንግሥት ተቃውሞ የሚያነሱ ሰዎች እርምጃ ይወሰድባቸው ነበር። ይህንንም አዝማሪዎች ያውቃሉ። ያም ሆኖ ግን አዝማሪዎች በዚህ ዘመንም አላረፉም። ፕሮፖጋንዳ ያራምዱ ነበር፤ የጦርነት መርዶ ነጋሪ ነበሩ። በዘፈኖቻቸውም እንዲህ ይሉ ነበር።
የፍየል ወጠጤ ትክሻው ያበጠ፤ ልቡ ያበጠበት
‹‹እንዋጋ!›› ብሎ ለነብር ላከበት!
የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች!
ንጉሳዊ ሥርዓትን አስወግዶ የመጣው ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ተቃዋሚዎች ነበሩት። ከእነዚህ ተፋላሚ ኃይሎች ጋር በነበረ ግብግብ ከፍተኛ ጭፍጨፋ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ከላይ የቀረበው የአዝማሪ ግጥም የመጨረሻ ስንኝ፤ ‹‹አብዮት ልጆቿን ትበላለች›› እየተባለ የሚነገረውን የደርግን ፍጻሜ ይነግረናል። የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ከአገር መውጣት የደርግ ፍጻሜ ይሆናል። ‹‹ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች›› የተባለው ለዚህ ይመስላል።
ካቻምናም እሮሮ ዘንድሮም እሮሮ
ዝም ነው ፀጥ ነው እሮሮን ዘንድሮ
ደርግ ንጉሳዊ ሥርዓቱን ያስወገደው፤ በዝባዥ ሆነ፣ ግፍ እና በደል አበዛ፣ ፍትህ ጠፋ… ብሎ ነው። ዳሩ ግን ይሄው ችግር በደርግ ሥርዓትም ተደገመ። አገዛዙ አፋኝ ሆነ። ከላይ ያለው ግጥም የሚነግረን ይህንኑ ነው። ባለፈው ሥርዓት እሮሮ ነበረን፤ አሁንም ይሄው እሮሮ ሆነ፤ አሁንስ ተስፋ ቆርጠን ካልተውነው ምንም መፍትሔ አላገኘንም የሚል ይዘት ያለው ነው።
በዚሁ በደርግ ዘመነ መንግሥት፤ አዝማሪዎች አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በግልጽ ይናገሩ ነበር። እንደሚታወቀው በደርግ ጊዜ የማርክሲስትና ሌኒኒስት ፍልስፍና አምልኮ ሆኖ ነበር። እዚህ ላይ አንድ ቀልድ ነግሬያችሁ ነው ወደ አዝማሪዎች ግጥም የምሄደው።
በደርግ ጊዜ በቀበሌ ገበሬ ማህበራት ስብሰባ እየተደረገ ነው አሉ። ሰብሳቢው ለገበሬዎች ሲያስረዳ ማርክስ እንዳለው፣ ኤንግልስ እንዳለው፣ ማኦ እንዳለው፣ ሌኒን እንዳለው… እያለ ያስረዳል። በየስብሰባው ‹‹እገሌ እንዳለው›› የሚል ገለጻ ያሰለቻቸው አንድ ገበሬ እጃቸውን አውጥተው ‹‹እኔ እምለው! እኒህ አባ እንዳለው የሚባሉ ሰውየ ግን ስንት ልጆች ነው ያሏቸው?›› አሉ ይባላል።
ይሄው የማርክስ እና የሌኒን ጉዳይ በአዝማሪዎችም እንዲህ ተብሎ ነበር።
ማርክስ እና ኤንግልስ ሌኒንም እያሉ
ማኦ ቼ ጉቬራ ሆ ቺ ሚኒ እያሉ
መሬትን ለአራሹ ይሰጠው እያሉ
የዘንድሮ ልጆች ብዙ ጉድ አፈሉ!
በደርግ ዘመን እንዲህ በግልጽ ይተች ነበር ማለት ነው። አዝማሪዎች የህዝብን ብሶት በማስተጋባት፤ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ነበሩ ማለት ነው። ተከታዮቹ ግጥሞች ደግሞ ተጨማሪ ማሳያ ይሆኑናል።
በእቅፍሽ ልውል ስል ክንድሽ እያፈነኝ
በካባሽ ላጌጥ ስል ክሳዱ እያፈነኝ
መናገሩን ፈቅደሽ በቀቀን ሁን ያልሽኝ
ባባትህ ተውና በእኔ ስም ማልልኝ
ብለሽ የገረፍሽኝ፤ ብለሽ የዘለፍሽኝ
ምየም አልጠቀምኩሽ እምቢም ብል ላተዪኝ
ምናለበት ነበር ያንቺ ልጅ ባልሆንኩኝ!
ፖለቲካዊ ሀሳቡ ለፍቅረኛ የተዘፈነ መስሎ ነው የቀረበው። በነገራችን ላይ ይህ አይነት አገላለጽ በኢህአዴግ ዘመን ባሉ ብዙ ዘፈኖች ውስጥ ይስተዋላል። ዘፋኞች ይህን አስበው ይዝፈኑት አይዝፈኑት ባይታወቅም ሰዎች ግን ተደራቢ ትርጉም እየሰጡ ‹‹እንዲህ ማለት ፈልጎ ነው›› ሲሉ ይሰማል። እርግጥ ነው ኪነ ጥበብ ለትርጉም ተጋላጭ ነው፤ በተለይም ግጥም ደግሞ በጣም ተጋላጭ ነው። ገጣሚው ራሱ ሌላ ጊዜ ቢያነበው ሌላ ትርጉም ሊወጣው ይችላል። ቢሆንም ግን አንዳንዶቹ ደግሞ ነገር በማጣመም ባይሆንም በግልጽ የሚታወቁም አሉ። ለምሳሌ ከላይ በቀረበው ግጥም ውስጥ ‹‹መናገሩን ፈቅደሽ በቀቀን ሁን ያልሽኝ›› የምትለዋ ስንኝ ምንም ነገር ማጣመም ሳይሆን በቀጥታ መንግሥትን የምትተች ናት። እንዲያውም ከደርግ ይልቅ ኢህአዴግን ትገልጻለች። በደርግ ጊዜ ፈቃድ ራሱ እንደሌለ ነው የሚወራው።
እንግዲህ ኢህአዴግም የአዝማሪ ትችት አልቀረለትም። ‹‹ከሌሎች በተሻለ፤ የመናገር ነፃነት ሰጥቻለሁ፣ የመገናኛ ብዙኃን እንደ አሸን ፈልተዋል›› ቢልም የህዝብ ብሶቶች ግን በአዝማሪዎች በኩል እንዲህ ደርሶታል።
አንዲት ጊደር ሸጬ፤ ኢገማ ከፍየ፤ አኢወማ ከፍየ
አኢሴማ ከፍየ
ለእናት አገር ጥሪ ለድርቅ ከፍየ
ግብር ታክስ ላምራቾች ሁሉ ከፍየ
አንዲት ብር ቀርታኝ ሽልጦ ልገዛ ዓይኔ እህል ሲራብ
መንጥቆ ወሰዳት ለወታደር ቀለብ
እንዲህ ያለ ጊዜ የዘመን ቆረንጮ
ወልዶ ለዘመቻ ሰርቶ ለመዋጮ
በነገራችን ላይ አጥኚው ያስቀመጣቸው ግጥሞች አንዳንድ ቦታ ላይ የመቀያየር ባህሪ ያላቸው ይመስላል። ለምሳሌ ከላይ የቀረበው ግጥም በደርግ ዘመን ያለ ባህሪ ይመስላል፤ ምክንያቱም ወላጆች ልጆቻቸውን በግዳጅ ለዘመቻ የሚልኩት በደርግ ዘመን ነበር። የመዋጮዋ ነገር ግን ኢህአዴግን በትክክል ትገልጻለች። ምናልባት ኢህአዴግም ከደርግ ቀጥሎ የመጣ ስለሆነ አያደርገውም ብለን መደምደምም አንችልም፤ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በማግባባትም ቢሆን ብዙ ወጣቶች ዘመቻ እንዲሄዱ ተደርጓል። እንዲያውም ራሱ አጥኚው እንደሚነግረን በኢህአዴግ ዘመን አዝማሪዎች ከተችነትም ሆነ ከአወዳሽነት ይልቅ ወደ ማዝናናት ያተኮሩበት ነው፤ ለዚያውም በባህል ምሽት ቤቶች ብቻ ተወስነው።
በእርግጥ ችግሩ የአዝማሪዎች እንዳልሆነ አጥኚው አንድ ነገር ነግሮናል። የባህል ምሽት ቤቶች ታዳሚዎች ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ግጥም አይወዱም፤ አዝማሪዎች ደግሞ በታዳሚው ፍላጎት ነው የሚጫወቱት። ‹‹ፖለቲካና ኤሌክትሪክን በሩቁ›› የሚለውን ሀሳብ የሚደጋግሙ ታዳሚዎች ናቸው ያሉት። እንግዲህ በኢህአዴግ ዘመን ከአዝማሪዎች ይልቅ ታዳሚው ፖለቲካን ፈርቷል ማለት ነው(ጠልቷል ማለት ይሻል ይሆን?)
የአጥኚው ግኝት እንዳለ ሆኖ፤ እኛ ግን ከምናስተውለው ነገር ተነስተን ሌላም ምክንያት ማስቀመጥ እንችላለን። አዝማሪዎች በባህል ምሽት ቤቶች የተወሰኑ ናቸው። የባህል ምሽት ቤት ደግሞ የሚሄደው ወጣት እንጂ ፖለቲከኛ አይደለም። ወጣቶች ፖለቲካ አይወዱም ባይባልም መዝናኛ ቦታ ላይ አይፈልጉትም ማለት ግን እንችላለን።
ወጣቶች ፖለቲካ አይወዱም የሚለውም ያስኬደናል። በምዕራባውያን ባህል የተበረዘ ወጣት ወደመዝናናቱ ነው የሚያተኩረው። ሲጀመር የምሽት ጭፈራ ቤትና የባህል ምሽት የሚሄዱት ብዙም ለፖለቲካ ቅርብ ያልሆኑትና መዝናናት ላይ የሚያተኩሩት ናቸው። ስለዚህ የባህል ምሽት ቤቶች ላይ በተሰራ ጥናት በኢህአዴግ ዘመን ህዝቡ ፖለቲካ ፈርቷል ወይም ጠልቷል ማለት አያስችልም።
እንዲህ የተባለውም በኢህአዴግ ዘመን ነው።
ወይ አልተጣላነ አልተደባደብነ
ሰተት ብለው መጥተው ቤት አፍርሱ አሉነ
ወንዱም አላረሰ ሴቱም አላረሰ
እንደ ጥንብ አሞራ ቤት እያፈረሰ!
ደርሶ ማንጎራጎር ልማዱ ነው ድሃ
እየቀዘቀዘው የሚጠጣው ውሃ!
ልክ በንጉሳውያኑ ዘመን እንደነበረው ትችት ይህ ግጥም ኢህአዴግን ብን አድርጎ የሚተች ነው። እንዲያውም በሰምና ወርቅ ተሸፍኖ ሳይሆን በግላጭ! በኢህአዴግ ዘመን በልማት ምክንያት የነዋሪዎች ቤት ሲፈርስ አይተናል። በቅኔ ለበስ ግጥሞችም እንዲህ ተብሏል።
የምን ጅዳ ጅዳ የምን ዱባይ ዱባይ
እንገድብሻለን አንችንም እንደ ዓባይ
መብራት ለምን ጠፋ እያልኩ የምቆጨው
ለካ ሻማ ሻጭ ነው ኃይል የሚያሰራጨው
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ስንኞች የሴቶችን ወደ አረብ አገር መሄዳቸው መነሻ አድርጎ ለሚወዳት የገጠመው ይመስላል፤ የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች ላይ ግን የመንግሥትን ነጋዴነት ይነግረናል።
እንግዲህ የአዝማሪነት ሚና በኢህአዴግ ዘመንም ፖለቲካን ይነካካ ነበር ማለት ነው። ሆኖም ግን አሁን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ወደ አዝናኝና አስቂኝነት ተቀይሯል። ለማዝናናትና ለማሳቅ ተብለው በባህል ምሽት ቤት የሚባሉ ግጥሞች ለመገናኛ ብዙኃን የማይመቹ ስለሆነ አልፈናቸዋል። አብዛኞቹ ወሲብ እና ሀፍረተ ሥጋ ላይ መሰረት አድርገው የሚባሉ ናቸው። በኪነ ጥበብ ዓይን ከታዩ ደግሞ፤ ነውርነታቸው ብቻ ሳይሆን የጥበብ ለዛም የላቸውም።
አጥኚው መፍትሔ ቢሆን ብሎ ያስቀመ ጠውን ጠቁመናችሁ ሀሳባችንን እንደምድም። የአዝማሪነት ሙያ ከቃላዊ ትውን ጥበብነት ወጥቶ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ቢጠና፣ በኪነ ጥበብ የትምህርት ክፍሎች በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ ቢሰጥ፣ አዝማሪዎች ልክ እንደ ሚዲያው ኢንዱስትሪ ቢታዩ፤ ይህን አገራዊ ጥበብ ዓለም አቀፍ እውቅና ያስገኘዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ዋለልኝ አየለ