መምህርት አመለወርቅ ገዛኸኝ በመምህርነት ሙያ ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በተማሪዎች ሥነ ምግባር ዙሪያ ብዙ ነገር ታዝበዋል፤ተመልክተዋል፡፡
የነገ ሀገር ተረካቢዎችን በሥነምግባር የማፍራት ኃላፊነት ባለባቸው በትምህርት ተቋማት ውስጥ መልካም ሥነምግባር ያላቸው ተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ ሲጋራ፣ጫት እና የመሳሰሉ አደንዛዥ እጾች ሱሰኛ የሆኑ፣ አልባሌ ቦታ የሚውሉ፣ ካለበቂ ምክንያት ከትምህርት ቤት የሚቀሩ፣ ኩረጃን ልምድ ያደረጉ እና የቡድን ጸብ ላይ የሚሰማሩ ተማሪዎችን ማየት የተለመደ ነው ይላሉ መምህሯ፡፡
ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው የሚያስቡ ተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ ሥነምግባር የጎደላቸው ተማሪዎች አሉ የሚሉት ለስምንት ዓመታት ያህል በመምህርነት ያሳለፉት መምህርት አመለወርቅ ገዛኸኝ፤ እሳቸው በሚያስተምሩበት ሆነ በሌላ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ከቤታቸው ሲወጡ የለበሱትን የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) መንገድ ላይ በሌላ ልብስ በመቀየር ትምህርታቸውን በመከታተል ፋንታ መገኘት በሌለባቸው አልባሌ ቦታ ሲያሳልፉ እንደሚታዩ ይገልጻሉ፡፡
ለዚህ ሥነምግባር የጎደለው ተግባርም የጓደኛ ጫና እና የቤተሰብ አስተዳደግ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አንስተው፤ የወላጆችና የመምህራን ያልተገባ የቁጥጥር ዘይቤም በተማሪዎች ዘንድ አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
የልጆችን በመልካም ስብእና ለማነጽ ወላጆችና መምህራን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው የሚናገሩት መምህሯ፤ ቤተሰብ ልጆቹን አቅርቦ ማናገር እና የእለት እለት እንቅስቃሴያቸውን መከታተል እንዲሁም መምህራን ለተማሪዎቻቸው አርአያ በመሆንና ቅርብ ግንኙነት በመፍጠር በሥነ ምግባር የታነጹ ሀገር ተረካቢዎችን ማፍራት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
ተማሪዎችን በሥነ ምግባር ለማነጽ ስድቦችንና አካላዊ ቅጣትን መጠቀም ተማሪዎቹን ለንዴት፣ እልኸኝነትና ስሜታዊነት የሚዳርግ መሆኑን አንስተው፤ ከዛ ይልቅ በሥነምግባር ጉድለት ሳቢያ ሊከሰትባቸው የሚችለውን ጉዳቶች በተረጋጋ ሁኔታ ማስረዳትና ወደ ትክክለኛው መስመር መምራት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
ተማሪዎችን በእውቀትና በሥነ ምግባር ለማነጽና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር ወላጆች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ፡፡
ለልጆቹ የሚያስብ ወላጅ ከሌለ ለራሱ የሚያስብ ወጣት መፍጠር አዳጋች እንደሚሆን የሚናገሩት ደግሞ የሥነልቦና ባለሙያና የህይወት ክህሎት አሰልጣኝ የሆኑት ወይዘሪት ፍረወይኒ ረታ ናቸው፡፡ እንደሳቸው አባባል፤ ቤተሰብ ወይም አሳዳጊ የኑሮ ሁኔታ፤ የልጆች በአስተዳደግ ወቅት ፍቅር ማጣት፣ የአትችሉምና የበታችነት ስሜት ልጆች ላይ መፍጠር በአጠቃላይ ከቤተሰብ ጋር በላላ ግንኙነት ያደጉና የኖሩ ተማሪዎች በአብዛኛው ወደ አልተገባ መንገድ እንዲገቡ የሚገፉ ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
ተማሪዎች በሌሎች ዘንድ እውቅና ለማግኘትና በሚሰማቸው የበታችነት ስሜት በጎ ወዳልሆነ ተግባር ለመሰማራት እና የአቻ ግፊት ውስጥ እንዲገቡ እንደሚያደርጋቸው ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች በመጠጥ ፣ በጫት እንዲሁም በሌሎች ሱስ አምጪ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል፡፡
በትምህርት ሰአታት ትክክል ባልሆነ መንገድ ከትምህርት ቅጥር ግቢ በመውጣት ቁማር ቤት የሚሄዱት በአብዛኛው የቤተሰብ ፍቅር እጦት ያለባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአሉታዊ የአስተዳደግ ዘይቤ ምክንያት ከባህልና ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ላልተገባ ነገር ሲያውሉ የሚስተዋል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በተማሪዎች ላይ የሚወሰዱ የቁጣና በዱላ የእርምት እርምጃዎች ተማሪዎችን ለእልህና ለበቀል ብሎም ሌላ ሰው ላይ ጫና ለማድረስ ከመሞከር ባለፈ መፍትሄ እንደማይሆን አንስተው፤ተማሪዎች ያልተገባ ባህሪ ቢያሳዩ እንኳን በምክርና በንግግር መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡
በትምህርት ሰአት ከትምህርት ገበታው ውጪ የሆነ ተማሪ ሲያገኝ ለመገሰጽ መምህር ወይም ወላጅ መሆን አይጠይቅም ያሉት ወይዘሪት ፍረወይኒ፤ ሁሉም በኃላፊነት ለምን ብሎ ከመጠየቅ ጀምሮ ስርአት እንዲይዙ መምከር አለበት ባይ ናቸው፡፡
የሥነልቦና እና የማህበራዊ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት ላቀው በበኩላቸው፤ ለተማሪዎች የሥነምግባር ችግር መንስኤ በዋነኝነት የወላጆች አስተዳደግ መንገድ ነው ይላሉ፡፡
አንዳንድ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥም ሆነ ከትምህርት ቤት ውጭ ባልተገባ ቦታና ጊዜ ለተለያዩ ሱሶች ተጋልጠው ይታያሉ፡፡ ለዚህም በእድሜ ከሚከሰት ባህሪ በተጨማሪ የወላጅ አስተዳደግ፣ የአቻ ግፊት፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሱስ ማዘውተሪያዎች መብዛት እና የትምህርት ቤት አስተዳደር ማነስ እንደምክንያት የሚጠቀስ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
አቶ ዳዊት እንደሚናገሩትም፤ ከወላጆቻቸው የሚሰጣቸው አላስፈላጊ ገንዘቦች ወደ ሱስ የሚ ያስገባቸው ሲሆን፤ ለሱሳቸው የሚሆን ገንዘብ የሌላቸው ደግሞ በስርቆት ላይ ይሰማራሉ፡፡
ይህን የልጆች ያልተገባ ባህሪ ደግሞ የመግራት የወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ኃላፊነት ነው፡፡ከቤት ውስጥ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ያላቸውን እንቅስቃሴ መከታተልና የባህሪ ለውጥ ሲያስተውሉ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ተከታትሎ በአጭሩ በመልካም ስብእና ማነጽ ይገባል፡፡ በተለይ ወላጆች በጣም ጥብቅ እና ልቅ ባልሆነ አስተዳደግ በሥነምግባር በትምህርታቸው ልጆቻቸውን የበቁ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡
የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች በመልካም ሥነምግባር ታንጸው ማደግ ለአንድ ሀገር ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመፍጠር ያስችላል፡፡ በመልካም ሥነምግባር የታነጹ ወጣቶችን ለማፍራትም ሁሉም ድርሻ ያለው ቢሆንም ቤተሰብ፣ትምህርት ተቋማት፣መገናኛ ብዙሀን እና የሃይማኖት ተቋማት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም