በመዲናዋ የሚከሰቱ የደንብ መተላለፎች 61 በመቶ ቀንሰዋል

– በሩብ ዓመቱ አንድ ሺህ 358 ሕገወጥ ግንባታ ላይ ርምጃ ተወስዷል

አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ የሚከሰቱ የደንብ መተላለፎችን በ61 በመቶ መቀነስ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡በሩብ ዓመቱ አንድ ሺህ 358 ሕገወጥ ግንባታ ላይ ርምጃ መውሰዱን ጠቁሟል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው ዓመት ሦስት ወራት ውስጥ የደንብ ጥሰትን በተሰራ የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ በከተማው የሚታዩ የደንብ ጥሰቶች 61 በመቶ ቀንሰዋል፡፡

ባለስልጣኑ ወንጀልና ደንብ መተላለፍ ከመፈጸማቸው በፊት የስልጠና እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት የተሠራና የተሻለ ለውጥ የመጣበት መሆኑን አንስተው፤ በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የባለስልጣኑ የስልጠና እና ግንዛቤ የማስጨበጥ አቅም ማደጉን ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የደንብ መተላለፍና ተያያዥ ሕገወጥ ተግባራትን የመከታተልና የመቆጣጠር ብሎም እርምጃ የመውሰድ ሥራ በትኩረት መሥራቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም አንድ ሺህ 358 ሕገወጥ ግንባታ፣ 14 ሺህ 300 በላይ ሕገወጥ ንግድ፣ ሁለት ሺህ 722 ሕገወጥ ደረቅ ቆሻሻ እና ፍሻሽ አያያዝ፣ ሦስት ሺህ 156 ሕገወጥ መንገድ አጠቃቀም ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡

እንዲሁም ሁለት ሺህ የሚጠጉ አዋኪ ድርጊቶች እና 40 ሺህ 425 ሕገወጥ ማስታወቂያ ላይ እርምጃ የተወሰደ መሆኑን አንስተው፤ ስድስት ሺህ 459 ካሬ መሬት ጥበቃ የተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በሩብ ዓመቱ የተደረገ የመሬት ወረራ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በበጀት ዓመቱ በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ከተለያዩ የደንብ መተላለፎች ቅጣቶችን ጨምሮ 42 ሚሊዮን 410 ሺህ በላይ ገቢ ብር ማስገባት መቻሉንም ገልጸው፤ ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ34 ሚሊዮን ብር ጭማሪ የታየበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም የከተማውን የኮሪደር ልማት መሰረተ ልማት የማስጠበቅ ኃላፊነት ከከተማ አስተዳደሩ ተረክቦ ያስተዳደረበት ሩብ ዓመት መሆኑን ሻለቃ ዘሪሁን ገልጸው፤ የከተማዋን ፅዳት ለማስጠበቅ በደንብ ቁጥር 167/2016 መሰረት ጠንካራ የደንብና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በከተማዋ የተሠሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በመጠበቅ ከተማውን ጽዱና ሰላም በማድረግ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ በመሥራት በሩብ ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ባለስልጣኑ በሩብ ዓመቱ በተቋም ግንባታ፣ የስልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስፋት በማከናወን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት መሆኑን አንስተው፤ የተሰጠውን የደንብ ጥሰትን የመከላከል፣ የመቆጣጠርና እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You