በሀገራዊ ምክክሩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕይታ

ዜና ሀተታ

በኢትዮጵያ ባህሎች ችግሮች ሲፈጠሩ ተቀራርቦ በመነጋገር ለችግሮቹ መፍትሄ ማበጀት የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ መደበኛ በሆነው የህግ አሰራር ሊፈቱና ሊቋጩ ላልቻሉ ጉዳዮች ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ በክልል ደረጃ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ እያካሄደ ነው። ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡

በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ፤ በክልሉ ከሚገኙ 57 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተቋማትና ማህበራት እንዲሁም የመንግሥት አካላትና የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ ለመሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ምን ዕይታ አላቸው? እና ተሳትፎአቸውስ እንዴት ይገለጻል? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክሩ ተሳታፊ ፓርቲ ተወካዮች ሃሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡

የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ እንደሚናገሩት፤ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሳታፊዎች ልየታ ጀምሮ ተሳትፈዋል፡፡ እንዲሁም እየተከናወነ በሚገኘው የአጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በክልሉ የሚገኙ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት ተሳትፈዋል ይላሉ፡፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ማናቸውም ቡድኖች ወደጫካ መግባት እንደሌለባቸው ያነሱት አቶ ሰለሞን፤ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮችን በውይይትና በንግግር ብቻ መፍታት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ ሲባል የሕዝቦችን ችግር በመፍታት የመፍትሄ አካል የሚሆን እንጂ ችግሮችን የሚያባብስ አይደለም፡፡ እነኝህ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሀገርን ወደ አንድነትና ትብብር የሚያመጡ ሃሳቦችን ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ይህ የምክክር ሂደት አንዱ ከአንዱ የሚማርበት፣ ሀገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ ሃሳቦች በነጻነት የሚገልጹበት አውድ መሆኑን አውስተዋል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰባስበው ያመጧቸውን አጀንዳዎች የሚያቀርቡበት አውድ ፈጥሯል፡፡ ለዚህም ኮሚሽኑ የቆመለት ዓላማ ከግብ እንዲመታ የጋራ ምክር ቤቱ ከማህበረሰብ ተወካዮች ምልመላ ጀምሮ በርካታ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የምክክር ሂደት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በመሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እድለኛ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ሰለሞን፤ ሌሎች ሀገራት ሀገራዊ ምክክር አድርገው ያልተሳካላቸው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በመኖሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ምክክር ተስፋ የሚጭረው መንግሥት ጣልቃ ከመግባት ይልቅ እራሱን ባለድርሻ አካል አድርጎ እየተሳተፈ መሆኑ ነው ይላሉ፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን የኢዜማ ፓርቲ የመንግሥት ክንፍ መሪና የዞኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ክፍሌ ሽፈራው በበኩላቸው፤ ሀገር የአንድ ሰው ወይም የጥቂት ቡድኖች ሳትሆን የሁሉም የጋራ መሆኗን በማንሳት፤ ለዚህም ለደረሰባት ችግር መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለው ሁሉም በነጻነት መመካከር ሲችል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ ክፍሌ ገለጻ፤ የምንመካከረው ሀገራችንን ከችግር በሚያወጡ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የምክክር ሂደቱ ጊዜውን የዋጀ ነው፡፡ የምክክር ሂደቱ ሁሉም ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር ለማድረግ በሚያስችሉ ሃሳቦች ዙሪያ መምከር የሚያስችል ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋናነት የሚፎካከሩት ሃሳባቸውን ለሰፊው ሕዝብ በማቅረብ ነው የሚሉት አቶ ክፍሌ፤ ሀገር የምትለማውና ሰላም የሚሰፍነው በሃሳብ ፍጭቶች እንጂ ጦር በመማዘዝ አይደለም። ከዚህ አኳያም ወደጫካ የገቡ ቡድኖችም የእውነትም ለዜጎቻቸው የሚታገሉ ከሆነ ዜጎች ወደ ተሻለ ለውጥ እንዲመጡ ሃሳቦቻቸውን ይዘው ወደ ኮሚሽኑ መምጣት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

አቶ ክፍሌ፤ ይህንን አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ሂደት ስንመኘው የነበረ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከመከፋፈልና ከመለያየት ይልቅ አንድነቷን ማጽናት የምትችለው በኢትዮጵያዊነት ላይ በተመሰረተ የፖለቲካ እሳቤ ስትመራ ነው፡፡ ለዚህም ሁሉም ፓርቲዎች በአንድነት ሲቆሙ የኢትዮጵያን ውድቀት የሚሹ አካላት ሴራቸው እንዲመክን ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚሰሩት የሕዝብን ችግር ለመፍታት እስከሆነ ድረስ በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የሚገልጹት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ሰብሳቢ ተመስገን ሰለሞን ናቸው፡፡

ኮሚሽኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳዎችን አሰባስቦ ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት አለን የሚሉት አቶ ተመስገን፤ ፓርቲያቸው አብን በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ኮሚሽኑ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ከተሳታፊዎች ልየታ ጀምሮ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

አቶ ተመስገን፤ ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱን እያከናወነ የሚገኘው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ችግር ባለበት ሁኔታ መሆኑን በማንሳት፤ በየቦታው የሚስተዋሉ ግጭቶችን በማስቆም ሰላምን ለማስፈን የምክክር በር ለመክፈት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You