– 287 ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል
አዲስ አበባ፡- ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ 250 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ መደበኛ ኮምፖስት እየተመረተ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ 287 ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውም ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና የምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ዓመት 250 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ መደበኛ ኮምፖስት የማምረት ሥራ የተጀመረ ሲሆን እስካሁንም 65 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ማምረት ተችሏል፡፡
እንደ አቶ ኤሊያስ ገለጻ፤ በዘንድሮው ዓመት አራት ሚሊዮን ኩንታል ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ (ቨርሚኮምፖስት) ለማምረት በእቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡
በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት በአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር 287 የተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ማዕከላት በሁሉም ወረዳዎች ላይ መገንባታቸውን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ጤናማ አፈርን ለትውልዱ ማስተላለፍ በሚያስችል መልኩ ማዕከላቱ ተገንብተዋል ብለዋል፡፡
በክልሉ የተቀናጀ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ያለው በመደበኛ ኮምፖስት 250 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ለማምረት ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ለሚስተዋለው የአፈር ለምነትና ጤንነት መቀነስ የመሬት መሸርሸር፣ የኬሚካል ማዳበሪያ ዋጋ መጨመር እና የአርሶ አደሩ መሬትን የመንከባከብ ባህል እያነሰ መምጣት እንደም ክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአፈርን ጤናማነትን ለመጠበቅ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በወረዳዎች የተገነቡትን ማዕከላት ተከትሎ ንዑስ ማዕከላት በየቀበሌው ተገንብተው ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ የገለጹት አቶ ኤሊያስ፤ አርሶ አደሮች ከባለሙያዎች በሚሰጣቸው ሙያዊ ድጋፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
እንደ ኦሮሚያ ክልል አማራጭ የምርት ማሳደጊያ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተለይም በመደበኛና በቨርሚ ኮምፖስት ላይ በስፋት እየተሰሩ የሚገኙ ሥራዎች አርሶ አደሩን ውጤታማ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም