የጨርቃጨርቅ ዘርፉን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፡- የጨርቃጨርቅ ዘርፉን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና መሠረተ ልማቶችን የማጠናከር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከ250 በላይ የፋሽን፣ ጨርቃጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት ኤግዚቢሽን ትናንት በአዲስ አበባ ተከፍቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የጨርቃጨርቅ ዘርፉን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና መሠረተ ልማቶችን የማጠናከር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ኤግዚቢሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥጥ፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ የተሰማሩ አካላትን ለማገናኘት እድል ይፈጥራል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካም የዘርፉን አሁናዊ ቁመና ለመቃኘት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ የጨርቃጨርቅ ዘርፉን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና መሠረተ ልማቶችን የማጠናክር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ተወዳዳሪና ውጤታማ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን በቴክኖሎጂ መደገፍና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ማሳደግ እንደሚገባ በመግለጽ፤ መድረኩ የእርስ በእርስ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፤ የባህል ጨርቃጨርቅና ፋሽን ኢንዱስትሪው ለቱሪዝሙ ዘርፍ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእጅ የሚሰሩ ጨርቃ ጨርቅ የማምረት ጠንካራ የተከበረ ባህል አላት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የባህል ጨርቃጨርቅ፣ የጥጥ አምራችነት በበርካታ ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ባህላዊ ጥበብ ነው ብለዋል፡፡

ፋሽን ዲዛይነሮችን፣ ጨርቃጨርቅ አምራቾችን፣ ሻጮችና የፋሽን ኢንዱስትሪው ተሳታፊዎች የዕደ-ጥበብ ስራቸው አስደናቂ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአለባበስ ባህል የማህበረሰብን ማንነት፣እምነት፣ባህልና ቦታ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ መልክዓ ምድሮች የሚኖሩ ከ80 በላይ ብሔረሰቦች እንዳላት በመግለጽ፣እያንዳንዳቸው ወጎች፣ ልማዶች፣ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ እምነትና የአለባበስ ዘይቤዎች እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የባህላዊ አልባሳት ዲዛይነሮች የፈጠራ ችሎታና ጥበብ የብዙዎችን ትኩረት መሳቡን ገልጸው፤ በቱሪዝም ላይ ጉልህ የሆነ አንድምታ ያላቸው በመሆኑ ሊጠበቁና ሊተዋወቁ ከሚገባቸው ቅርሶች መካከል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪስት መስህቦችና አስደናቂ የቱሪዝም አቅሞች ባለቤት ናት ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ባህል፣ አልባሳት፣ የጨርቃጨርቅ ምርቶችንና ሀገር በቀል ክህሎቶች ጎብኚዎችን ለመሳብ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

በሀገር በቀል የጨርቃ ጨርቅ ምርቶቻችን ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ እንደ የቱሪስት መስህብነት ማስተዋወቅና ለአምራቾች የሚያመጡትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ኤግዚቢሽኑ የንግድ ትስስር፣ ምርቶችን ለማስተዋወቅ፣ መስተጋብር ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን በመግለጽ፣ የኢንዱስትሪ ትስስር ለመፍጠር፣በጨርቃ ጨርቅና ፋሽን እሴት ሰንሰለት ላይ አጋርነት ለማጠናከር እድሎችን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

10ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግና ፋሽን ሳምንት ለአምስት ቀናት እንደሚቆይና ከ30 ሀገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ የፋሽን የጨርቃጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You