አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚከበረው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግሥት ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል፡፡
አርባ ምንጭ የተለያዩ ብሔሮች በአብሮነትና በወንድማማችነት ተቻችለው የሚኖሩባት ከተማ ናት ያሉት ኃላፊዋ፤ የከተማው ሕዝብ ለ19ኛ ጊዜ ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል እንግዶቹን ለመቀበል ደማቅ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት በዓሉን በልዩ ሁኔታ ለማክበር የተለያዩ ኮሚቴዎችን ማቋቋሙን ገልጸው፤ የመሰረተ ልማት፣ የአካባቢ ውበት ሥራ፣ የአደባባይ ማክበሪያ፣ የፓናል ውይይት ማድረጊያ ቦታዎችን፣ የሆቴል ዝግጅትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ መቀየቱን ገልጸዋል፡፡
የከተማውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከነዋሪዎች ጋር ውጤታማ ሥራ መሠራቱን የጠቆሙት ወይዘሮ ሰናይት፤ በዚህም የኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።
በዓሉ በክልሉ መከበሩ የክልሉን የቱሪዝም ጸጋዎች ለማስተዋወቅና ለማልማት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል አርባ ምንጭ ከተማ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን እንዳላስተናገደች የሚናገሩት ኃላፊዋ፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለማክበር የባሕል አምባሳደር ሆነው ወደ ከተማዋ የሚመጡ ዜጎችን በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።
ከከተማው የሆቴል ባለቤቶች ጋር ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መካሄዱን ጠቅሰው፤ ሁሉም ሆቴሎች እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን እንዳሳወቁ ጠቁመዋል።
በከተማዋ የሚከበረውን ሀገር አቀፍ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ከኅዳር 20ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ባሉ ቀናት ለመቀበል የሚያስችል መርሐ ግብር መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።
ከበዓሉ ጎን ለጎን የከተማዋን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማሳየት ጥረት እንደሚደረግ አመላክተው፤ በአሁኑ ጊዜ ከተማዋ ውጤታማ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲከበር የክልሉ ሕዝብ እንዲሁም የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች የኢትዮጵያዊ ባህልን መሰረት ባደረገ መልኩ እንግዶችን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ወይዘሮ ሰናይት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አማን ረሽድ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም