ከኮሪደር ልማት በፊት ስለነበረችው አዲስ አበባ ታሪክ ነጋሪ አያስፈልገንም:: የአባቶችና እናቶች ምስክርነት አያስፈልገንም:: ምክንያቱም፤ ይህ አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላ ታሪክ ነው:: ከኮሪደር ልማቱ በፊት የነበረችውን አዲስ አበባ ‹‹ትናንት›› ለማለት ለአቅመ ማገናዘብ መድረስ ብቻ በቂ ነው:: ትንሽ ታሪክ ለማስመሰል ግን ሦስት ዓመት እንኳን ወደኋላ መለስ እንበልና ጥቂት ማሳያዎችን እንውሰድ::
ከፓርላማ መብራት አንስቶ በቤተ መንግሥቱ በኩል ወደ ሸራተን እና ካዛንቺስ ለመሄድ በቀኝ በኩል ያለውን የእግረኛ መንገድ መያዝ ግድ ነው:: ይህ ገና ሦስትና አራት ዓመት ብቻ የሆነው ታሪክ ነው:: በዚህ መንገድ ላይ ለማለፍ የሰርከስ ልምምድ ሳያስፈልግ አይቀርም ነበር:: አስፋልቱን እና የእግረኛ መንገዱን በምትለየዋ ቀጭን ጠርዝ ላይ እየተንጠለጠሉ ማለፍ የግድ ነበር::
በዚች ቀጭን ጠርዝ ላይ የሚሄድ ሰው ጉዳይ ኖሮት በችኮላ የሚሄድ ሳይሆን፤ ‹‹በዚች ጠርዝ ላይ አልፋለሁ አታልፍም›› ውርርድ ተወራርዶ የሚጫወት ነው የሚመስለው:: ምናልባትም ከርቀት ሆኖ የሚያስተውል ሰው ‹‹ትልቁ ሰውዬ ምን ያጃጅለዋል?›› ሊል ይችላል:: ትልቁ ሰውዬ ግን እንደዚያ የሚሄደው ወዶ ሳይሆን ወይም ለጨዋታ ብሎ ሳይሆን የሚረግጠው ስላልነበረው ነው:: ወደ አስፋልቱ መኪና፣ ወደ እግረኛ መንገዱ ደግሞ ኩሬ ስለሆነ ነው::
ይህንንም የሚያደርጉት ወጣትና ጎልማሳ የሆኑ ጤነኛ ሰዎች ናቸው:: በዕድሜ የገፉ ሰዎች የነበራቸው ዕጣ ፋንታ ቀሚሳቸውን ወይም ሱሪያቸውን ከፍ አድርገው ይዘው፤ በውሃ እየተንቦጫረቁ ማለፍ ነው፤ ለዚያውም ለማለፍ ወረፋ ይዘው ማለት ነው:: የነበረው ችግር ውሃና ጭቃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እንደዚያም ሆኖ ጠባብ ነበር:: ወረፋ ይዞ ተራ በተራ የሚታለፍ ነበር:: ዛሬስ?
ዛሬ ከፓርላማ መብራት እስከ ካዛንቺስ ድረስ የሚሄድ ሰው የሚያየው ውብ ነገር ዓይን አዋጅ ሆኖበት ሳያስበው ራሱን ሸራተን ጋ ሊያገኘው ይችላል:: ካዛንቺስ ለመሄድ ትምህርት ሚኒስቴር ጋ ታክሲ ጥበቃ ዝናብ ወይም ፀሐይ ይመታው የነበረ ሰው፤ ዛሬ ግን ‹‹እባክህ ና በነፃ ልውሰድህ›› ቢሉት እሺ አይልም! ምክንያቱም በየመንገዱ የሚያየው ነገር ይበልጥበታል::
አሁን ደግሞ እነሆ ተራው የካዛንቺስ ሆኖ፤ ካዛንቺስ እየተሰራች ነው:: ካዛንቺስ ከመናኸሪያ አካባቢ ጀምሮ እስከ ቶታል፤ ከዚያም እስከ ሐናን ዳቦ እና ዑራኤል የነበረው ትርምስ የትናንት ትዝታ ነው:: ከመናኸሪያ ወደ ቶታል የሚወስደው መንገድ (በተለምዶ ሰንደይ ማርኬት የሚባለው) ሰው እና ተሽከርካሪ ወረፋ ይዞ የሚተላለፍበት ነበር:: ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣና የሚሄድ ብቻ ሳይሆን፤ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚሄዱ ሰዎች ራሱ ወረፋ ይዘው የሚተላለፉበት ነበር:: ስለዚህ በዚያ ሁኔታ እስከ መቼ ይቀጥላል?
አሁን ደግሞ ግማሽ ዓመት እንኳን ያልሞላው ታሪክ እናስታውስ:: ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳ ለመሄድ እስከ ራስ መኮንን ድልድይ ድረስ የነበረውን የእግረኛ መንገድ አስቡት:: ልክ ሸራተን አካባቢ እንዳለው የሰርከስ ልምምድ የሚደረግበት የሚመስል ነበር:: ድንጋይ ድንጋይ እየረገጡ፣ እየተንቀጠቀጡ የሚታለፍ ነበር::
ከዚያችውም ጠባብ የእግረኛ መንገድ ላይ ደግሞ ትንንሽ ንግድ ቤቶች ነበሩበት:: አደናቅፎት ዘመም ያለ ሰው ዕቃ ላይ ሊወድቅ ይችላል:: የአስፋልቱ ጥግ ላይ ደግሞ ባለቤቶቻቸው የት እንደሄዱ የማይታወቅ የቆሙ ተሽከርካሪዎች አሉ:: በዚህ የሲዖል መንገድ በሆነ ቀጭን መተላለፊያ ላይ ለማለፍ ወረፋ መጠባበቅ የግድ ነበር:: የእግር መርገጫን አትኩሮ በማየት በጥንቃቄ ማለፍ ነው:: በአካባቢ የሚገኙ ነገሮችን አያለሁ ብሎ ዓይኑን ወደ ጎን የሚል ካለ መውደቁ አይቀሬ ነው:: ዛሬስ?
ዛሬ ከአራት ኪሎ ፒያሳ ለመሄድ ‹‹ምን ጉዳይ አለህ?›› አይባልም:: መንገዱን ለማየት መሄድ በራሱ ጉዳይ ነው:: እዩኝ እዩኝ ይላል:: ያ እየተንጨዋለሉ የሚታለፍ መንገድ፣ እጅን ከኪስ ከቶ ወደፈለጉበት እያዩ የሚጓዙበት ሆኗል:: ለማለፍ ወረፋ የሚጠባበቁበት ሳይሆን አራትና አምስት ሆኖ ጎን ለጎን መሄድ የሚቻልበት ሆኗል:: ለጤና አስፈላጊ ነው የሚባለውን የእግር ጉዞ ለማድረግ የሚያነሳሳ ብቻ ሳይሆን የሚያስገድድ ሆኗል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በፓርላማ እንደተናገሩት፤ ለአንድ ሚሊዮን ባለመኪና አስፋልት መንገድ ተሰርቶ፣ ለአምስት ሚሊዮን እግረኛ ግን ትኩረት አልተሰጠም ነበር:: በዚያ ላይ መኪና ያለው ሁሉ ለአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ሁሉ ሞተር ሊያስነሳ አይችልም:: ለጤናም ሆነ ለቅልጥፍና በእግር መሄድ ግዴታ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ:: ለሻይ እና ለምሳ ሲወጣ ሁሉ መኪና ሊያስነሳ አይችልም:: ስለዚህ የእግረኛ መንገዶች ማማራቸው ሊመሰገን የሚገባ ነው::
ለመሆኑ ግን ትናንት ምን ስንል ነበር?
ዛሬ ላይ የኮሪደር ልማቱ በመሰራቱ እያማረረ ያለው ሁሉ ትናንትም ሲያማርር ነበር፤ ምን እያለ? ‹‹የእግረኛ መንገድ የለም›› እያለ! ‹‹አዲስ አበባ ተግማማች›› እያለ:: እንዴት የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም የዲፕሎማት መቀመጫ ሆና… እያለ የሚያማርረው ብዙ ነበር:: ከዓመታት በፊት የነበሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ትልቁ ብሶት የከተማዋ መንገዶች መበላሸት፣ የወንዞች ዳርቻ መጥፎ ሽታ፣ በየመንገዱ ያሉ ቤቶች ደረጃቸውን አለመጠበቅ፣ የሸራ እና የዛገ ቆርቆሮ ክምችት ነበር:: እነዚያ ብሶቶች፣ እነዚያ ወቀሳዎች፣ እነዚያ አቤቱታዎች ሰሚ አግኝተው ዛሬ ተቀርፈዋል:: ስለዚህ አዲስ አበባ ዛሬ የምንመኛት ሆናለች ማለት ነው::
ለመሆኑ አዲስ አበባ ነገ ምን አይነት ትሆናለች?
የዛሬውን የኮሪደር ልማት ያመሰገንነው፣ ያደነቅነው፣ ከትናንት አንፃር ነው:: ስለዚህ የዛሬው ውበት ለነገው ትውልድ አደራ የሚሰጥ ይሆናል ማለት ነው:: የነገውን ትውልድ የሚያነቃ ይሆናል ማለት ነው:: አንድ ጥሩ ነገር ሲጀመር ትልቁ ጥሩነቱ አርዓያ መሆኑ ነው:: ቢያንስ ቢያንስ ከዚህ የተሻለ እንኳን ባይሰራ፣ ከዚህ የባሰ አይደረግም ማለት ነው:: የትናንቱን አይነት አናይም ማለት ነው:: ዛሬ እንዲህ አይነት ከተሰራ ነገ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ይሰራል ማለት ነው::
የነገዋ አዲስ አበባ ከዚህም ትበልጣለች ማለት ነው:: ዛሬ ለናሙና ያህል በአራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ከመገናኛ እስከ ሲ ኤም ሲ፣ ቦሌ፣ መስቀል አደባባይ… በአጠቃላይ በከተማዋ ዋና ዋና መስመሮች ያየናቸው ውብ ሥራዎች ነገ ደግሞ በመላዋ አዲስ አበባ ይሆናል ማለት ነው:: በአንድ ዓመት ውስጥ ይህ ሁሉ ከተሰራ፣ በሚቀጥሉት ዓመታት የምትሰራው አዲስ አበባ ከዚህም በላይ ትሆናለች ማለት ነው:: አራት ኪሎን ወይም ቦሌን አይቶ ወደ ሰፈሩ ሲሄድ ቅር የሚለው ሰው፤ ነገ ሰፈሩም እንደነ ቦሌ ይሆናል ማለት ነው:: ልጆቹ ከተማ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ ማለት ነው::
ከዓመታት በፊት ስለአዲስ አበባ የነበረውን ትርክት ማስታወስ በጣም ቀላል ነው:: በእንግድነት ብቻ የሚያውቋት የክፍለ ሀገር ሰዎች ሳይቀር ‹‹አዲስ አበባ›› ሲባል ወደ አዕምሯቸው የሚመጣ መጥፎ ሽታ ነበር:: ከተማ ሲባል ከመጥፎ ሽታ እና ከመንገድ መጨናነቅ ጋር የሚያያዝ ምስል ፈጥሮ ነበር:: አሁን ግን አዲስ አበባ ለማየት የምታጓጓ፣ ሌሎች ከተሞችንም ለመሥራት የምታነሳሳ ሆናለች ማለት ነው:: ነገ ለመላው ኢትዮጵያ ከተሞች የንጽህና እና የውበት አርዓያ ትሆናለች ማለት ነው:: የነገዋ አዲስ አበባ ከዛሬዋ በላይ አዲስ ትሆናለች!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም