አዲስ አበባ፡- በ16ኛው የተባበሩት መንግሥታት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ ሀገራት የብዝሀ ህይወት ሀብታቸውን ለመታደግ በበርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ሲል የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
በ16ኛው የተመድ የ2024 የብዝሀ ህይወት ጉባኤ “COP 16” አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማሪዮ (ዶ/ር) ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የጉባኤው ሀገራት የብዝሀ ህይወት ሀብታቸውን ለመታደግ በበርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ያደረጉበት ነው ብለዋል፡፡
ከስምምነቶቹ መካከል «ካሊ ፈንድ» የተሰኘ ዓለም አቀፋዊ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ ስምምነት ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ስምምነትም ከዲጂታል ሴኩዬንስ መረጃ (ዲ.ኤስ.አይ) ጥቅማ ጥቅሞችን ለመጋራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የካሊ ፈንድ ስምምነት ዋነኛው ጥቅም የመድኃኒት፣ የመዋቢያ፣ የባዮ ቴክኖሎጂ፣ የእንስሳት እና የእፅዋት እርባታ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች ጥቅሞቹን ለታዳጊ ሀገራት እና ለአካባቢው ማህበረሰቦች እንዴት ማካፈል እንዳለባቸው የሚመለከት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በጉባኤው ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ በርካታ ሃሳቦች ላይ ተወያይታለች። በዚህም ኢትዮጵያ መልካም ትብብሮችን ማጠናከር ችላለች ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ካነሳቻቸው ሃሳቦች ውስጥ በዋናነት ለታዳጊ ሀገራት ለብዝሃ ህይወት ጥበቃ ፈንድ ሊደረግ ይገባል የሚል ጉዳይ ላይ በትኩረት ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በጉባኤው አፍሪካ የሀብት አሰባሰብ ሥርዓት ውስጥ መግባት አለባት የሚል ጉዳይ መነሳቱንም ገልጸዋል።
የአፍሪካ መነሻ ያላቸው ማህበረሰቦች ብዝሃ ህይወትን ባህላቸውና መብታቸው እንዲጠበቅና የቋንቋ እውቅና ሰነድ መጽደቁ እንደ ውጤት የሚታይ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሌሎች ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ አፍሪካዊያን (African Descendents) ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤዎችን የሚያካትት እንዲሁም በብዝሀ ህይወት ጥበቃ እና ዘላቂነት ባለው አጠቃቀም ላይ የሚጫወቱትን ጉልህ ሚና እውቅና የሚሰጥ ተጨማሪ ውሳኔም መተላለፉን አስረድተዋል፡፡
በጉባኤው የተወሰኑ ጉዳዮች በይደር ለማየት ስምምነት ላይ ቢደረስም፤ የኩሚንግ ሞንትሪያል የብዝህ ህይወት ማሕቀፍን አተገባበር ለማሳለጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በ16ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2024 የብዝሀ ህይወት ጉባኤ “COP 16” በኮሎምቢያ ካሊ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል። ኢትዮጵያም በጉባኤው ስድስት ልኡካን በመላክ መሳተፏ ይታወቃል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም