አዲስ አበባ፡- በሲዳማ ክልል 192 ኪሎ ሜትር የገጠር ልማት ኮሪደር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
በሲዳማ ክልል የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደስታ ዳንጮ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሲዳማ ክልል 192 ኪሎ ሜትር የገጠር ልማት ኮሪደር ስራ በማህበረሰቡ ተሳትፎ እየተካሄደ ነው፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ በሲዳማ ክልል በእቅድ ደረጃ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ እየተገባ መሆኑን አስታውቀው፤ በመጀመሪያ ዙር የገጠር ልማት የኮሪደር ስራም በፈጣን መንገድ መስመሮች በተለይም ሀገር አቋራጭ አስፋልቶች ያሉበት አካባቢና ክልልን ከክልል የሚያገናኙ መስመሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም አንደኛው ከሀዋሳ እስከ ዲላ የሚገኘው የፈጣን መንገድ መስመር ላይ ሲሆን ይህም 80 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም ከአቦስቶ እስከ ኩላ ቦሬ ድረስ የሚገኘው 46 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መስመር እና ከሀዋሳ አለታወንዶ እስከ በዳዬ በንታ የ66 ኪሎ ሜትር አስፋልት መስመር ላይ ማህበረሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ ነው ያለው ብለዋል፡፡
በዚህም በማህበረሰብ ተሳትፎ መንገድ ዳር ያለው የምንጠራ ስራ በስፋት እየተሰራ ሲሆን መንገድ ዳር ላይ ገባ ብለው የገነቡት እንዲያፈርሱ፣ አጥር ያጠሩት እንዲያነሱና የተተከሉ ዛፎች እንዲነሱ፤ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ ስራዎችን የማድረግና ቤት የማፍረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ ለአካባቢው ውበትና ጽዳት፣ በአረንጓዴ ልማት ስራ የሀገር በቀል ዛፎችን ጎን ለጎን ለመትከል የሚያስችል፣ ለአካባቢው ነዋሪ ኑሮን የሚያቃልልና የሚያዘምን መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል በክልሉ የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በአራቱም ዞኖች የንቅናቄ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ በተለይም ለአካባቢው ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተው፤ በዚህም የኢኮኖሚ መነቃቃት፣ ለተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በተለይም የገጠሩ ጠጠር መንገድ ማህበረሰቡ እርስ በእርስ እንዲገናኝ እና የተሳለጠ እንቅስቃሴ ለመፍጠር የሚያስችል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
እስካሁን ካለው የገጠር ልማት ኮሪደር ስራ በሕዝብ ተሳትፎ እየተሰራ እንጂ በመንግሥት የተያዘ በጀት አለመኖሩን አንስተው፤ በቀጣይ በቀጥታ ከመንግሥት በጀት ተመድቦለት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ በተለይም በክልሉ በሚሰሩ ረጃጅም እና የጠጠር መንገዶች አካባቢ ለማስጀመር እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም