የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል

አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ። የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ ከዓለም አቀፉ ኖውማን ካፌ ግሩፕ ጋር ተፈራርሟል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ ከዓለም አቀፉ ኖውማን ካፌ ግሩፕ ጋር ትናንት ሲፈራረም እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ቡና ምርታማነት ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው። የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል።

ስምምነቱም ከአርሶ አደሮች እስከ ተጠቃሚዎች ድረስ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ሀገሪቱ ከቡናው ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚሠራ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ስምምነቱ በሄክታር የሚገኘውን የቡና ምርት መጠን ለማሳደግ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የአመራረት ሂደትን ለመከተል ይረዳል።

በሀገር ደረጃ የቡና ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቷል። በዚህ ልክ የግሩፑ የቡና እርሻ መሬትን ምርታማነት ማሳደግ ይገባል። ለዚህም ሲባል ኖውማን ካፌ ግሩፕ ጋር ስምምነት ፈጽመናል ያሉት አቶ ጀማል አህመድ፤ ስምምነቱ ቴክኒካል ድጋፍና የገበያ ተደራሽ ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለቡና ምርት ምቹ ሀገር ነች። ይህንን አቅም ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እንሰራለን ያሉት ደግሞ የኖውማን ካፌ ግሩፕ ሥራ አስፈፃሚ ዴቪድ ኖውማን፤ የኢትዮጵያን ቡና ታሪካዊ አመጣጥ በማስተዋወቅ የገበያ ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

የምንሠራው ሥራ ቡናን በምርት መጠን፣ በጥራት እና በተደራሽነት ደረጃ ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ ኖውማን ካፌ ግሩፕ 60 ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈና በ26 ሀገራት በቡና ገበያ የሚታወቅ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ስምምነቱም ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፈ የኢትዮጵያ ቡናን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ስምምነቱም ከወረቀት ያለፈና በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ዘርፉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You