ኢንዱስትሪዎችና የቢዝነስ ተቋማት አሰሪና ሠራተኛን የሚያገናኙ መድረኮች እንዲፈጥሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፡- ኢንዱስትሪዎችና የቢዝነስ ተቋማት በየዘርፋቸው አሰሪና ሠራተኛን የሚያገናኙ መድረኮችን መፍጠር አለባቸው ሲሉ በሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ጥሪ አቀረቡ።

ደረጃ ዶት ኮም እና ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ያዘጋጁት ዐውደ ርዕይ ሲከፈት በሚኒስቴሩ የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት፤ አሰሪና ሠራተኛን በቀጥታ የሚያገናኙ መድረኮች መስፋፋት አለባቸው።

ዐውደ ርዕዩ ኢንዱስትሪውን የማነቃቃት፣ የሀገር ጉልበት የሆነውን ወጣት ወደስራ ለማሰማራት እንዲሁም ሀገር ተወዳዳሪና ኢኮኖሚዋ እንዲጠነክር ለማድረግ አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ተመሳሳይ ዐውደ ርዕዮች በዓመት አንዴ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በክልሎች፣ በወረዳዎች፣ በዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ለወጣቱ ተደራሽ እንዲሆኑ በየጊዜው በማዘጋጀት ኢንዱስትሪዎችና የቢዝነስ ተቋማት በየዘርፋቸው አሰሪና ሠራተኛን የሚያገናኙ መድረኮችን መፍጠር አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በስራ ላይ የሚገኙ ፖሊሲዎች በርካታ የስራ ዕድል በሚፈጥር መልኩ ተዘጋጅተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሚመለከታቸው ተቋማትም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ፈርጀ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ገንብቶ ስራ ላይ ማዋሉንም አስታውሰዋል።

ቴክኖሎጂው የስራ ገበያ መረጃን በማቀላጠፍና የሰው ኃይል አቅርቦት እና ፍላጎትን በማጣጣም ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

ዕድሜያቸው ለስራ የደረሱ ዜጎች፣ ወደስራ የገቡ ኢንተርፕራይዞች እና ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በተዘጋጀው የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት በመመዝገብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉና ተጠቃሚ እንዲሆኑም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በዚህ የመረጃ ስርዓት ተመዝግበው የነበሩ ከ43 ሺህ በላይ ወጣቶች ወደስራ እንዲገቡ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በተጨማሪ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የመረጃ ተአማኒነት ችግር እንደሚቀርፍ ገልፀዋል።

ጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ከማደራጀት አንስቶ፣ በሚፈልጉት ዘርፍ እንዲሰለጥኑ ማድረግ፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን የፋይናንስ አቅርቦት፣ የቦታ ወይም የሼድ አቅርቦትን እንደሚያመቻችና ለሌሎች ስራ አጥ ወጣቶችም የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You