አዲስ አበባ፡- የቱሪዝም ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ሽግግር የሚገባውን ድርሻ እንዲያበረክት ለማድረግ የፖሊሲ ክለሳ መደረጉን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ገለጹ፡፡ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ፖሊሲ ክለሳ ላይ ያተኮረ ምክክር መድረክ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ቢሮ ተወካዮች ጋር ትናንት ተካሂዷል፡፡
አቶ ስለሺ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት፤ የቱሪዝም ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ሽግግር የሚገባውን ድርሻ እንዲያበረክት ለማድረግ እና ከሀገራዊ ቁልፍ አጀንዳዎችና የልማት እቅዶች ጋር ለማስተሳሰር እንዲቻል የፖሊሲ ክለሳ ተደርጓል፡፡
በ2001 ዓ.ም የወጣውን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፖሊሲ መከለሱን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ቱሪዝም በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዓለም አጠቃላይ ጥቅል ምርት 10 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የቅድሚያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ቱሪዝም እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
ዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስገኝና ኢኮኖሚው ላይ ያለው አበርክቶ እንዲያድግ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በነባሩ ፖሊሲ ያጋጠሙ ጉድለቶችና የፖሊሲ ክፍተቶችን መቅረፍ፣ ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ሽግግር የሚገባውን ድርሻ እንዲያበረክት ማስቻል፣ ከሀገራዊ ቁልፍ አጀንዳዎችና የልማት እቅዶች ጋር ለማስተሳሰር የፖሊሲ ክለሳ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ፖሊሲው ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ ተቋማዊ አደረጃጀትን በማስተካከል፣ የሕግ ማሕቀፎችን ለመቅረፅ እና የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ በቱሪዝም ሴክተር እና በሌሎች የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች ቅንጅት ማሳደግ፣ ዓለም አቀፍ ክስተቶችን እና ውጫዊ ሁነቶችን ባገናዘበ መንገድ ዘርፉን መምራት ለፖሊሲ ክለሳው በተጨማሪ ምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ረቂቅ የፖሊሲ ክለሳ ዝግጅት መከናወኑን አመላክተው፤ በተከታታይ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ይደረግበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሂደትም የሚገኙ ግብዓቶችን በማከል ፖሊሲው ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡
በምክክር መድረኩ አዲሱ ረቂቅ ፖሊሲ ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን፤ ተሳታፊዎችም ቢካተቱ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡
የቱሪዝም ፖሊሲ ክለሳው በ2026 ዓ.ም ተወዳዳሪ፣ ዘላቂና ፈተናዎችን የሚቋቋም የቱሪዝም ዘርፍ በመፍጠር ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ተመራጭ መዳረሻዎች መካከል አንዷ ሆና ማየት የሚል ራዕይ አንግቦ የተቀረጸ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም