ሀዋሳ:- የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማጽናት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቸሩጌታ ገነነ ገለጹ።
አቶ ቸሩጌታ ይህን ያሉት ትናንት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ነው። እሳቸው እንዳሉት እንደ ሰላም ሚኒስቴር ሲዳማ ክልል አስተማማኝ ሰላም ያለበት ክልል መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
የሲዳማ ሕዝብ ሰላምን የኖረበትና ጠንቅቆ የሚያውቀው በመሆኑ ሰላሙን ለማፅናትና ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ አንስተዋል።
ለዚህም በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የፖሊስ ጽህፈት ቤቶችና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ማሳያ ናቸው በማለት፤ ይህም ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮ መሆን የሚችል ስራ ነው ብለዋል።
በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በአመራሩ ያላሰለሰ ጥረት የተገነቡት ማዕከላት የህብረተሰቡን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው ያሉት አቶ ቸሩጌታ፣ ማዕከላቱ በተለይም በቴክኖሎጂ የተደገፉ በመሆናቸው ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል ማህበረሰቡ ዘላቂ ሰላም እንዲኖረው የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
በሰላም ኮንፈረንሱ የተገኙት የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት፤ ባለፉት አራት ዓመታት የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ሰፊ ስራ ተሰርቷል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ የፀጥታ መዋቅርን ማጠናከርና የፀጥታ ተቋማትን መገንባትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የማህበረሰቡ ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይም ይኸው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሁሉም ሰው ለሀገር ሰላም ዘብ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም