የወጪ ንግድ ዕድገቱ ምንጮች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ወቅት ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የወጪ ንግድ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን አስታውቀዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ የተገኘው ውጤት ማስቀጠል ቢቻል እንኳን በዓመት አምስት ቢሊዮን መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያ በዘርፉ ካላት እምቅ አቅም አኳያ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑንም ያመላክታሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ በሚቀጥሉት ዓመታት 50 እና 100 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ መሠራት አለበት ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡

በዘርፉ የተገኘው ውጤት ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ጋር ግንኙነት አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ውጪም ባለፉት ሶስት ወራት ስድስት ነጥብ አራት በመቶ ብልጫ ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱን የፋይናንሻል ሥርዓት መሻሻልና በትይዩ ገበያው መካከል ያለው ክፍተት ሰፊ እንዳይሆን መሠራቱ ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆናቸውንም ነው ያከሉት፡፡

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ለገሰ እንደሚሉት፤ በቅርቡ የተሻሻለው የማክሮ ኢኮኖሚ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪው በገበያው እንዲወሰን መደረጉ ለተገኘው ውጤት የጎላ ድርሻ አለው፡፡

ማሻሻያው መደረጉ ላኪዎች የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ ተለያየ ሀገራት ገበያ ሲልኩ ከሌላው በላይ የመወዳደር እድል ስለሚሰጣቸው የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ለማደግ ምክንያት ነው የሚሉት ባለሙያው፤ በዚህ የተነሳም ያደጉ ሀገራት ዋጋቸው እምብዛም እንዳይጨምር እንደሚያደርጉ ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነትም ጃፓን፣ ቻይና ደቡብ ኮሪያ አንድ የአሜሪካ ዶላር ከ120 እስከ አንድ ሺህ 300 ድረስ ይመነዘራል፡፡

በሩብ ዓመቱ የወጪ ንግድ 132 በመቶ ወይም ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጨምሯል ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በዓመት ኤክስፖርት ተልኮ የሚገኘው ገቢ ነዳጅ ገቢ ለማድረግ እንኳን የሚሸፍን አለመሆኑን ያክላሉ፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፎርሙ ከመካሄዱ በፊት ወርቅ የሚሸጥለት አጥቶ ከዓለም ገበያ እስከ 72 በመቶ ጨምሮ ይገዛ ነበር፡፡ በተጨማሪም የቀንድ ከብቶች በጎረቤት ሀገራት በኩል በሕገወጥ መንገድ ኤክስፖርት ይደረጉ የነበረውን ወደ ትክክለኛው ማሕቀፍ እንዲመጡ አድርጓቸዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ የተሻሻለው የባንኮች ዶላር መግዣና መሸጫ መካከል ያለው ልዩነት ከሁለት በመቶ እንዳይበልጥ መወሰኑ ለኢኮኖሚው ማሻሻያ ተጨማሪ እድል ይዞ የሚመጣ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ብሔራዊ ባንክ የመሪነት ሚናውን በማጠናከር ከዚህ የበለጠ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ማሻሻያው እንደተደረገ ባንኮች በአንድ ዶላር ያተርፉ የነበሩት አንድ ብር ከ90 ሳንቲም አካባቢ ቢሆንም በ15 ቀናት ልዩነት ውስጥ 12 ብር ደረጃ አድጎ እንደነበር ጠቅሰው፤ ይህም አስመጪው ያመጣው ዕቃ ላይ ጨምሮ ስለሚሸጥ ጉዳቱ ለህብረተሰቡ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ አስመጪና ላኪዎችን ሊጎዳ የሚችል ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ህብረተሰቡ ከመጎዳቱ በፊት ቀድሞ ኢኮኖሚውን እያነበበ መሰል ውሳኔዎችን መውሰድ እንዲሁም አስመጪዎች ዶላር ለመግዛት ሲፈልጉ ለባንኮች የሚከፍሏቸው የኮሚሽን ክፍያዎች ግልጽ ሆነው መነሻና መድረሻ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

አሁን ላይ በዘርፉ የተገኘው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው ብሔራዊ ባንክ በተለይ የንግድ ባንኮች የብድር አቅርቦት እና የዶላር ፍሰት ላይ እየሰሩ ያሏቸው ስራዎች ምንድነው፤ አካታችነታቸውስ ምን ያህል ነው የሚሉት ላይ ማጣራት አስፈላጊ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እንደ ሀገር ለብድር ከቀረበው ብር ውስጥ ከ23 በመቶ በላይ የሚሆነው 10 የሚሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች ብቻ መውሰዳቸውን ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክት ያስረዳሉ፡፡

ማሻሻያው በተለይ ዜጎች መቋቋም የማይችሉት የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም አስመጪዎችን በከፍተኛ ደረጃ የጎዳ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ የተገኘው እምርታዊ ለውጥ ከባለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ ሲደረጉ የነበሩ ማሻሻያዎች እንጂ በኢኮኖሚው ማሻሻያ የመጣ ነው የሚል ግምት እንደሌላቸው የገለጹት ደግሞ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና የፖሊሲ አማካሪ ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የዚህኛው ማሻሻያ ግን ውጤቱን ለማግኘት የተወሰኑ ጊዜያት የሚፈልግ ነው የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ይሁን እንጂ ማሻሻያው ካፒታል ገበያውን ለማሳደግና የውጭ ኩባንያዎች ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚችሉበት ሁኔታ እየፈጠረ ነው ይላሉ፡፡

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ ከማሻሻያው ጎን ለጎን ሰላምና ጸጥታው የሚረጋገጥ ከሆነ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልበት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከሚላኩ ምርቶች በተጨማሪ ሌሎች ለኤክስፖርት የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት አምርቶ መላክ ያስፈልጋል፡፡

ብዙ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ከቢሮክራሲ ጋር በተያያዘ ምሬት ሲያሰሙ ይስተዋላሉ ያሉ ሲሆን፤ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠልም ቢሮክራሲ ማስወገድ፣ ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም ሰፋፊ የምርመራ ዘገባዎች መሠራት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You