አዲስ አበባ፡- የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርናን ማረጋገጥ ለዘላቂ የምግብ ዋስትና መሰረት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ከጥቅምት 26 ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው ‹‹ከረሃብ ነጻ ዓለም›› ዓለም አቀፍ ጉባዔ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ትናንት ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሀገራዊ ሪፎርም አማካኝነት ለአየር ጠባይ ለውጥ የማይበገርና ቀጣይነት ያለው የምግብ ምርታማነትን ለማረጋገጥ ውጤታማ ሥራ እያከናወነች ነው ብለዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፃ፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድርቅና መሰል ችግሮች የማይፈትኑት ኢኮኖሚ በመገንባት ቀጣይነት ያለው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በግብርና ማሻሻያ ላይ ትኩረት ሰጥታ በመሥራቷ ድርቅን መቋቋም የሚችል እንደ ስንዴና ማሽላ ያሉ ሰብሎችን በመዝራት ምርታማነት ማሳደግ ችላለች፡፡
በተለይም 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ምቹ የግብርና ምህዳር ተፈጥሯል፤ ከዚህ ቀደም የማይታረሱ የነበሩ መሬቶችን በማረስ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ስትራቴጂክ አጋርነትን ይፈልጋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ፕሮግራም ቀርጻ እየሠራች እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ተላቃ ወደ ውጭ መላክ መጀመሯን ገልጸዋል፡፡
ከጉባዔ ተግባራዊ ምላሽ የሚሹ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። በዚህም ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተለይም ለሴት አርሶ አደሮች የሚደረገው ድጋፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፤ ረሃብ የተባበረ ዓለም አቀፍ ምላሽን ይፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ የተቀናጀ ምላሽ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ የተለመደውን የግብርና ዘዴ መቀየርን ጨምሮ ድርቅን መቋቋም የሚችሉና ምርታማ የሆኑ ዘሮችን በመዝራት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ረሃብን ማስወገድ የጋራ ጥረትን የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ከረሃብ ነጻ ዓለም ለመፍጠር የሚከናወኑ ሥራዎችን የሚደግፍ ዓለም አቀፍ ፈንድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በፖሊሲና በስልጠና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ግብርናን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ የምግብ ዋስትናን በቀጣይነት ለማከናወን በቴክኖሎጂ፣ በስልጠና፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ግብርና አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
አነስተኛ አርሶ አደሮች ለዓለም የምግብ አቅርቦት የጀርባ አጥንት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴን ወደ ዘመናዊ እንዲቀይሩ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡ እንዲሁም አካታች የፋይናንስና የገበያ ሥርዓትን መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም