“በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ስኬቶች እየተመዘገቡ ናቸው” – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አስታውቀዋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአዲስ አበባ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባኤ የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ስኬቶችም እየተመዘገቡ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝም የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ግብርናን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

መንግሥት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማጠናከርና ለማዘመን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ገልጸው፤ በዚህም ኢትዮጵያ የገጠማትን የምግብ ዋስትና ችግር መፍታት የሚያስችል ጉዞ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

ግብርናውን በምርምር ከመደገፍ በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዱ የሰብል አይነቶች እየለሙ እንደሚገኙ አመልክተው፤ በዚህም ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ራሷን በምግብ ለመቻል የሚያስችላት ጉዞ ላይ ናት ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ የዓለም ችግር የሆነውን ረሃብ ለማስወገድ ከጋራ ጥረት ጎን ለጎን ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና አጥጋቢ የፋይናንስ ድጋፍ መኖር እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ከርሃብ ነፃ የሆነ ዓለምን ለመፍጠር የፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን አውስተው፤ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚከናወኑ ሥራዎች ሕዝብን ለማስተባበርና ለማሳተፍ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

ረሃብ አልባ ዓለምን ተግባራዊ ለማድረግ የአፍሪካ ሀገራት በቂ በጀት መመደብና ራሳቸውን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ማብቃት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ፤ ረሃብን ከዓለም ለማስወገድ በአፋጣኝ ወደ ተግባር መግባት ተገቢ ነው፡፡ የምግብ ዋስትናንና የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ትብብር ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን በቴክኖሎጂና በፋይናንስ መደገፍ ከረሃብ ነጻ ዓለምን ለመፍጠር አጋዥ ነው፡፡

አፍሪካ እምቅ አቅሟን አሟጣ በመጠቀም አስከፊውን ረሃብ ለማስወገድ በአንድነት መነሳት አለባት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ረሃብን መዋጋት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ከረሃብ ነፃ ዓለም ለመፍጠርና ተግባራዊ እርምጃዎችን ወደ ውጤት ለመቀየር ባለራዕይ መሪዎችን ማብዛትና ትርክትን መቀየር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ጉባኤው የዘላቂ ልማት ግቦችንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንቅፋት የሆኑ ችግሮች የተለዩበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You