ዜና ሐተታ
አቶ ዓለሙ እንደሻ ይባላሉ። የመንጃ ጎሳ አባል ናቸው። አቶ ዓለሙን ከሸካ ዞን ማሻ ወረዳ በባሕልና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካይ በመሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኅብረተሰብ ተወካዮችና የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ ሲሳተፉ ነው ያገኘናቸው።
አቶ ዓለሙ፤ በውይይቱ በርካታ ሀገራዊና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ አጀንዳዎች እያደራጁ ስለመሆናቸው ገልጸው፤ አጀንዳዎቹ ተቀባይነት አግኝተው ወደ ተግባር ከተቀየሩ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርጉ እና ወደሚፈለገው ብልፅግና ማማ ላይ እንድትወጣ የሚያስችሉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
በምክክሩ ምንም አይነት የሀሳብ እና ነፃነት ገደብ ሳይኖር እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል ተወካይ ለአጀንዳ የሚሆን ሀሳብ እያቀረበ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ዓለሙ፤ የሀሳብ ግጭቶችንም በማስማማት ወደሚያግባባ ሀሳብ በመምጣት የምክክር ሂደቱ እየተካሄደ መሆኑን ያነሳሉ።
ወክለው የመጡትን የማኅበረሰብ ክፍሎች በባሕላቸውና በሙያቸው እየደረሰባቸው ያለው መገለል በውይይት እንዲፈታ ሀሳባችንን እያቀረብን ነው። አሁን ላይ በሀገር ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ለየት የሚያደርገው ታችኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ባካተተ መልኩ እየተከናወነ በመሆኑ ነው፤ ለዚህም ችግሮቻቸው እንደሚፈቱ እምነት እንዳላቸው አቶ ዓለሙ ያመላክታሉ።
እንደ አቶ ዓለሙ ገለጻ፤ የምክክር ኮሚሽኑ ማንም አካል ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ችግሮቻችንን እንድንናገር ዕድል ሰጥቶናል። ችግር ተፈጥሯዊ በመሆኑ መከሰቱ አይቀርም፤ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርገው የአንዱን ባሕልና የአኗኗር ዘይቤ የበታች በማድረግ የራስን ማጉላት አንዱ ምክንያት ነው። የትላንትና መጥፎ ታሪካችንን አስወግደን በመልካም እሳቤዎችን መተካት አለብን።
አቶ ታመነ ኃይሌ እንደ አቶ ዓለሙ ከካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ በባሕልና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወክለው አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ ተሳትፎ እያደረጉ ነው። አካል ጉዳተኛም ቢሆኑ ሕይወትን ለማሸነፍ የእንጨትና ብረታብረት ሥራዎችን በመሥራት እንደሚተዳደሩ ይናገራሉ።
በዚህ የምክክር ሂደትም ቀርበው በሚሠሯቸው ሥራዎችና በባሕላቸው ምክንያት መገለል እየደረሰባቸው እንደሆነ መናገራቸውን የሚያወሱት አቶ ታመነ፤ የሀሳብ መለያየቶች ተፈጥሯዊ ናቸው፤ ለዚህም ጎራ በመያዝና በዘፈቀደ ሳይሆን ተቀራርቦ በመነጋገር ወደአንድ ሀሳብ መምጣት ይቻላል ይላሉ።
አቶ ታመነ በምክክር ሂደቱ የሀሳብ ነፃነትን መሠረት በማድረግ ሀሳባቸውን እያቀረቡ ስለመሆናቸውና ምክክሩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ለውጥ አምጪ መሆኑን በመጠቆም፤ በምክክሩ የሚነሱ አጀንዳዎች በትክክል ተደራጅቶ በተገቢው ከተሠራና እንደሀገር ውጤታማ መሆን ይቻላል ነው ያሉት።
እንደ አቶ ታመነ ገለጻ፤ በምክክሩ ሀገሪቱን ሊገነቡ የሚችሉ ሀሳቦችን ተሳታፊዎች በነፃነት እያነሱና በጋራ በመመካከር አጀንዳዎቻቸውን እያጠናከሩ ነው። በዚህም እንደሀገር የጋራ ችግሮቻችን ምን እንደሆኑ በመለየት ውጤት ለማምጣት የመንግሥት እና የኅብረተሰቡ ድርሻ የጎላ ነው።
ይህ ሀገራዊ ምክክር ሀገራዊ ሠላምንና አንድነትን የሚያመጣው ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍል የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል በሚል ሀሳቡን አንፀባርቆ መፍትሔ ማግኘት ሲችል ነው የሚሉት ደግሞ ከምዕራብ ኦሞ ዞን ባቹማ ወረዳ በባሕልና በሙያቸው ምክንያት የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወክሎ የተሳተፉት ወይዘሮ የትምወርቅ ፍቅሩ ናቸው።
ወይዘሮ የትምወርቅ የሚኖሩበት የሜኒት ማኅበረሰብ ሸክላ በመሥራት የሚተዳደር ሲሆን ይህ ሀገራዊ ምክክር እንደሀገር ያሉብንን ችግሮች እንድንፈታ ያግዘናል። ሰላም ካለ መሥራት፣ መማርና መለወጥ ይቻላል። ለዚህም በምክክሩ ሀሳቦቻችንን እያንሸራሸርን ነው ይላሉ።
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራችን እስከአሁን የነበሩ ችግሮችን በንግግርና በምክክር ለመፍታት ኮሚሽኑ የጀመረው ጥሩ ጅምር መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ የትምወርቅ፤ ከቤተሰብ ጀምሮ በመመካከር እና በመደማመጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ይናገራሉ።
እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሀሳብ አፍኖ ከሚኖር ይልቅ ሀሳቡን እንዲገልጽ መደረጉ እጅጉን የሚያስደስት ነው። ከዚህ ቀደም ዜጎች ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ብዙም አመቺ ሁኔታዎች አልነበሩም የሚሉት ወይዘሮ የትምወርቅ፤ በአሁን ወቅት ዜጎች በሀገራቸው ሠላም እንዲሰፍን ሀሳብ እንዲያዋጡ ዕድል መሰጠቱ አስደሳች መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም