የኢትዮጵያ ግብርና በአመዛኙ የዝናብ ጥገኛ ሆኖ መቆየቱ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች አለመሟላት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የመሬት መራቆት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንቅፋት ከሆኑ ምክንያች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ እንደ ሌማት ትሩፋት፣ የከተሞች የከተሞች ግብርና ተግባር ላይ ውለዋል፡፡ በተከናወኑ ተግባራት በሰብል፣ በእንስሳትና በጓሮ አትክልት ልማት እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተገኙ ይገኛሉ፡፡ እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች፣ የእለት ምግብን ከማረጋገጥ በተጨማሪ፣ ዜጎች ሥራ መፍጠር እንዲችሉና የግብርና ምርት ተጠቃሚዎች በቀጥታ ከአምራች ገበሬው ጋር እንዲገናኙ አስችሏል፡፡ በከተማ ግብርና ዘርፍም ዜጎች በራሳቸው ጓሮ የራሳቸውን ምግብ ፍጆታ ከማምረት አልፈው ለገበያ እያቀረቡም ይገኛሉ፡፡
በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ አበባየሁ ላሊማ፣ በመኸር ወቅት የከተማ ግብርናን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስኬድ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በከተማዋ ባሉ 32 ገጠር ቀመስ ቀበሌዎች በእርሻና በእንስሳት ዘርፍ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በመሬት ላይ በሚሠራ የጓሮ አትክልት ልማት 5 ሺህ 595 ሰዎችን ያሳተፈ ሥራ ለመሥራት እቅድ ተይዞ በታቀደው መሬት ላይ አስፈላጊ ዘር መዘራቱን የተናገሩት ኃላፊው፤ ምርት ዘርና አስፈላጊ ማዳበሪያዎችም ጥቅም ላይ በመዋላቸው የሚፈለገው ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመለክታሉ፡፡
በከተማ ደግሞ በ7ቱም ክፍለ ከተሞች በእቃ ላይ አትክልት የማልማት ሥራዎች እየተሠሩ የሚገኝ ሲሆን፣ 346ሺ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ከ340ሺ በላይ ችግኞችን፣ በእቃ ላይ መትከል ተችሏል፡፡ በከተማ በመሬት ላይ ልማት 50 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ በመንግሥትና በግል ተቋማት፣ በጤና ተቋማትና እና በትምህርት ቤቶች ላይ ከ48 ነጥብ 9 ሄክታር ማልማት ተችሏል ይላሉ፡፡
ከጓሮ አትክልት ልማት የሚፈለገውን ያህል ምርት ለማግኘት አስፈላጊ ክትትልና እንክብካቤ እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በተለይም በሽታ እንዳይጠቁ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል በክረምት ወራት የተመረቱ ምርቶች በመድረሳቸው ገበያን ከማረጋጋት አንጻር፣ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በገበያ ላይ ያለው የምርት እጥረትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ከቀይ ሽንኩርት አንጻር ግን እጥረት መግጠሙን ያነሱት ኃላፊው፤ በቀጣይ በበጋ መስኖ ፕሮግራም ቀይ ሽንኩርት ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
በእንስሳት እርባታ ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተም ኃላፊው እንደገለጹት፣ የእንስሳት ልማት ዘርፍ ከምግብ ዋስትና፣ ከገበያ አቅርቦት እንዲሁም ከምግብና ሥነ ምግብ ጉዳዮች አኳያ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ እንደመሆኑ የምርት ጥራትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል፣ በዚህም በርካታ የእንስሳት ዝርያዎችን ማሻሻል የተቻለ ሲሆን፣ በተለይም የወተት ምርት ላይ በተሠራው ሥራ በቂ የወተት ምርትን ለከተማዋ ነዋሪ በተሻለ መጠን ማቅረብ ተችሏል፡፡
በዶሮ እርባታ ዘርፍም፣ ከአንድ ቀን ጫጩት ጀምሮ የተለያዩ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ወጣቶች በማስተባበር የዶሮ ምርትን ላይ ሰፋፊና ለውጥ ያስገኙ ሥራዎች መሠራታቸውን አቶ አበባየሁ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው እንደገለጹት፣ አምራቾች ያመረቱትን ምርት ሳይቸገሩ ተጠቃሚው ጋር የሚያደርሱበት ሁኔታም ተመቻችቶላቸው ምርታቸውን አውጥተው የሚሸጡባቸው ቦታዎችም ተመቻችቶላቸው ምርታቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ከሥራ ዕድል ፈጠራም አንጻር በርካታ በከተማዋ ያሉ ወጣቶች የግብርናውን ሥራ ውጤታማነት እያዩ ሙያዊ ምክርና ድጋፎችን በመጠየቅ በግብርና ተግባር ላይ ለመሠማራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙም በማንሳት፣ በገጠር ቀመስ ቀበሌዎችም ሆነ በከተማ ግብርና የሚከናወኑ ተግባራት የእያንዳንዱ ቤተሰብ ሕይወት የሚለወጥበት በመሆኑ ባለሙያው ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ተገቢው ግብዓት እንዲቀርብላቸውና ሥራዎች በዕቅድ መሠረት እንዲፈጸሙ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ያሉት ኃላፊው፤ ከእቅድ ወደኋላ መቅረትን ፈጽሞ እንደማይቻል አድርገን ለሀገራችን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየመራን ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የሥነ ምግብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ፈቃዱ ረታ እንደሚሉት “በተለይ በከተማ በትንሽ መሬት ላይ የሚከናወነው የግብርና ልማት ሥራ ኢኮኖሚን ከመደገፍ ባለፈ ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ከፍተኛ ድርሻ አለው ይላሉ። የከተማ ግብርና ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን በማጎልበት ጤናው የተጠበቀ አምራች ትውልድ እንዲፈጠር የሚያግዝ ነው ያሉት።
እንደ ሀገር መንግሥትም ለሥራው ትኩረት መስጠቱ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ስለሚያሳድግ ልማቱን ውጤታማ ያደርገዋል። በአሁኑ ጊዜ መንግሥት በትኩረት እያከናወነ ያለውን ሥራ በምርምር መደገፍና ቀጣይነት እንዲኖረው ማገዝ ያስፈልጋል ሲሉ ይገልጻሉ።
ዜጎች ከዚህ ልምድ ወስደው ባላቸው መሬት ላይ ልማቱን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ነው መምህር ፈቃዱ ያመለከቱት። ቶሎ የሚደርሱና በየጊዜው ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ አትክልቶችን አልምቶ በብዛት መመገብ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል በኩል ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ የከተማ ግብርናን ልማድ አድርጎት እንዲቀጥል ደግሞ ከዘር አቅርቦት ጀምሮ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና ግንዛቤ የማሳደግ ሥራን ተከታታይነት ባለው መልኩ ማጠናከር እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም