የኢትዮጵያን የሚቲዎሮሎጂ መሠረተ ልማቶች የሚያዘምን ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፡የኢትዮጵያን የሚቲዎሮሎጂ መሠረተ ልማቶች ማዘመን የሚያስችል ፕሮጀክት የሚተገበር መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር የሚተገብረውን የዓለም አቀፍ መሠረታዊ ምልከታ አውታር ፕሮጀክት በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ለዓለም አቀፍ መረጃ ልውውጥ የምትጠቀምባቸውን በሰው የሚሠሩ 16 የገጸ ምድር የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሰው አልባ (አውቶማቲክ) የሚቀይር ነው፡፡

በተጨማሪም የመረጃ ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ተጨማሪ 13 አዳዲስ የገጸ ምድር አውቶማቲክ የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎችን ማቋቋምን የሚያካትትም መሆኑን ገልጸው፤ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት መሠረተ ልማቶች ለማዘመን እና ለማስፋፋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር የተመደበለት እና በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚጠናቀቀው የዓለም አቀፍ መሠረታዊ ምልከታ አውታር ፕሮጀክት ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ከተለያዩ አጋር አካላት በተገኘ ድጋፍ ይከናወናል።ፕሮጀክቱን ለማስፈጸምም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአጋርነት እንደሚሠራ እና የኖርዌይ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሙያዊ የማማከር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የአየር ሁኔታ መከታተያ ጣቢያ በማቋቋም የምትሰበስባቸውና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የምታጋራቸው የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማጠናከር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የከፍታ አየር የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያን በተመለከተ ቀደም ሲል የነበሩንን ዘመናዊ የሚያደርግ እና ተጨማሪ ሦስት አዳዲስ የከፍታ አየር ጣቢያን ለማቋቋም፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን የሚያሟላ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚተገበረው የገጸ ምድር ጣቢያዎቹ በየ200 ኪሎ ሜትር ርቀት መላ ኢትዮጵያን እንዲሸፍን ሆኖ የተሰራጨ ሲሆን፤ የከፍታ አየር ጣቢያውም በ500 ኪሎ ሜትር ኢትዮጵያን እንዲሸፍን በአዲስ አበባ፣ በነገሌ ቦረና፣ በመቀሌ፣ በጅግጅጋ እና በጋምቤላ እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ መረጃዎችን ያለማቋረጥ በመሰብሰብና ለዓለም በማጋራት እንዲሁም ከመላው ዓለም የሚሰበሰብ መረጃን በመቀበልና በመተንተን የአየር ሁኔታ መረጃ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ፣ በአሕጉር አቀፍ እና ሀገራዊ የአየር ትንበያ ሞድሎች ውስጥ መረጃዎቹ እንዲካተቱ በማድረግ የትንበያ ትክክለኛነትና ጥራት ለማሳደግ ፕሮጀክቶች ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም የተሻሻለ ትንበያና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ አገልግሎት በመስጠት የአየር ፀባይ ለውጥን የመቋቋም አቅምን ይጨምራል ብለዋል።

በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ከአደገኛ የአየር ሁኔታና ፀባይ ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የፓሪስ ስምምነትንና የዘላቂ ልማት ግብን ለማሳካት፣ የሚቲዎሮሎጂ ምልከታን ለማጠናከርና ለማዘመን፣ ለዓለም አቀፍ መረጃ ልውውጥ እና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You