ቢሮው በብልሹ አሠራርና ሌብነት ላይ የጀመረውን ርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ በሚሰጠው የኦንላይን አገልግሎት ላይ በሚከሰቱ ብልሹ አሠራርና ሌብነት ላይ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ብልሹ አሠራሮች እና በሐሰተኛ አካውንቶች የወጡ ንግድ ፈቃዶችን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ጥበቡ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ቢሮው በከተማዋ ፈጣንና ቀልጣፋ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን በሚሰጠው የኦንላይን አገልግሎት ላይ በሚከሰቱ ብልሹ አሠራርና ሌብነት ላይ የጀመረውን ርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል።

ቢሮው የኦንላይን አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ለቁጥጥር አመቺ ለማድረግ ከወረዳ ጀምሮ በአንድ ሺህ 200 ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበሩትን አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በ26 ባለሙያዎች ብቻ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።

ቀደም ባሉ አካውንቶች የተሰጡ አገልግሎቶችን ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራዎች መሠራታቸውን አቶ ፍስሐ ገልጸው፤ በተሠራ የማጣራት ሥራም ከእውቅና ውጪ በሰባት ክፍለ ከተሞች 339 ሐሰተኛ አካውንቶች ሕገወጥ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ማረጋገጥ መቻሉን አብራርተዋል።

የተሳሳተ አካውንት በመክፈትና በመተባበር ተሳታፊ የሆኑ ፈጻሚዎችን በሕግ እንዲጠየቁ፣ አስተዳደራዊ እርምጃና በዲሲፕሊን እንዲጠየቁ እንዲሁም አለአግባብ የተከፈቱ አካውንቶች እንዲዘጉ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

እንዲሁም በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ 130 ሺህ በላይ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የተሰጡ ሲሆን በተሠራ የማጣራት ሥራም 362 በላይ አገልግሎቶች አሠራርን ባልጠበቀና መስፈርትን ሳያሟሉ አገልግሎት መስጠታቸውን ተረጋግጧል ብለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 32 የሚሆኑ አገልግሎቶች ዋና ዋና የሚባሉና የመንግሥትን ጥቅም ሊያሳጡ የሚችሉ አገልግሎቶች በ15 ፈፃሚዎች በተሰጣቸው ኃላፊነት መስፈርት የማያሟላ አገልግሎት የሰጡ እና ባልተሰጣቸው ኃላፊነት ሕገ ወጥ ሥራ የሠሩ ናቸው።

በአጠቃላይም ከ430 በላይ አገልግሎቶች መስፈርት ሳያሟሉ መሰጠታቸውን እና የተሳተፉ 131 ፈጻሚዎችና አመራሮች ተጠያቂ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም መሰል ሕገወጥ አካውንቶች እንዳይከፈቱ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ቴክኖሎጂውን ይበልጥ በማዘመን ብሎም የአገልግሎት ኦዲቱም ቀጣይነት ባለው አግባብ የማስኬድ ሥራ የሚሠራ መሆኑን አቶ ፍስሐ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ቢሮው የሚሰጡ አገልግሎቶችን ኦዲት በማድረግ በብልሹ አሠራርና ሌብነት ላይ የጀመረውን እርምጃና ተጠያቂነት የማስፈኑን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You