የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓትን በማጠናከር ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትን ማስፈን ይገባል

አዲስ አበባ፡የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓትን በማጠናከር ፍትሐዊና ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትን ማስፈን እንደሚገባ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ በሀገራዊ የአዕምሯዊ ንብረት ጉዳዮች ዙሪያ ከፖሊሲ አውጪዎችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንትናው ውይይት አካሂዷል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል እንደገለጹት፤ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓትን ማጎልበት ከተቻለ የንግድ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት ማጠናከር ይቻላል።

የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ምዝገባ በፈጠራ ሥራዎች ላይ ቁልፍ ሚና ቢኖረውም በሚጠበቀው ልክ ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ስምምነቶችን በመፈጸም ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ከቻለች የፈጠራ ሥራዎችን ማብዛት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፍ የአዕምሮ ንብረት ስምምነቶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየቀረቡ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር በማይጋጭ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም የአዕምሯዊ ንብረት ባለሀብቶች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡና ሥራ ላይ እንዲያውሉ ያግዛል ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በዘርፉ ለሚያከናውናቸው የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃና ልማት ሥራዎች እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶቹ በቂ ትኩረትን ሊሰጠው፣ ተቋማዊ አቅሙን እንዲያድግ፣ የሕግ ማዕቀፎችን እንዲሻሻሉና የአፈጸጸም ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎችና ምርምሮች በአግባቡ የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ሊካሄድላቸው ይገባል ብለዋል። የፈጠራን ሥራዎች በሀገር ውስጥ፣ በአሕጉር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ፈጠራና ቴክኖሎጂዎች መነሻቸው የማኅበረሰቡ ዕውቀት፣ ባሕልና ዕሴት በመሆኑ የአንድ ሀገር የሥልጣኔ ምሶሶዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በኢትዮጵያ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች፣ ምሑራንና ተመራማሪዎችን በማሳተፍ በተለያዩ መስኮች በሚሠሩ የፈጠራና ቴክሎጂዎች ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየት እንደጀመሩ ገልጸዋል።

የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሥርዓት ፈጠራን በማበረታታት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማመቻቸት፣ ፍትሐዊና ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትን በማስፈን ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ከሚያስተዳድራቸው ስምምነቶች መካከል የናይሮቢና የማራካሽ ስምምነቶችን መፈረሟን ገልጸው፤ ይህም በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ሚና ለመጫወት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በንግድ ኢንሸስትመንትና በሌችም መስኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንደሚረዳት አብራርተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የሚያስተዳድራቸውን አዋጆች ለማሻሻል እና ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማፀደቅ የሕግ አውጪ አካላትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና የማይተካ በመሆኑ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You