ወይዘሮ አዳነች አብቼ ይባላሉ፡፡ የኮልፌ ቀራንዮ የወረዳ ዘጠኝ ነዋሪ ሲሆኑ የአምስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ አጥንትን ከሚሰረስር የጠዋት ብርድና የፀሐይ ግለትን ተቋቁመው በአነስተኛ ንግድ ተሠማርተው የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ የሚሞሉ ብርቱ እናት ናቸው፡፡
ወይዘሮ አዳነች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከውጣ ውረዱ የሕይወት ልፋትና ድካም በላይ የሚያስጨንቃቸው አንድ ነገር ነው። እሱም እሳቸውና ልጆቻቸው የሚኖሩበት ቤት ለመፍረስ ቋፍ ላይ በመድረሱ ነው። በዚች ቤታቸው ጣራ ላይ የወደቀው የተላላጠ የኤሌክትሪክ ገመድ እሳት እየፈጠረ ማስቸገሩና ዝናብ በጣለ ቁጥር ወደ ቤት የሚገባው ጎርፍም ሌላው የሚያስጨንቃቸውና እረፍት የነሳቸው ጉዳይ ነው።
ዛሬ አልያም ነገ ልጆቻችን ጎርፍ ይወስዳቸዋል፤ በቤቱ ጣራ ላይ የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመዱ በንክኪ እሳት ፈጥሮ ይፈጃቸው ይሆን የሚለው ሀሳብ በሥራ የደከመ ሰውነታቸው በመኝታ ሳያርፍ ዓይናቸው በእንባ እንዲታጠብ አድርጎኝ ቆይቷል ይላሉ። ከሁሉም ቤት ውስጥ ወልዳ የተኛችና የአዕምሮ ዘገምተኛ የሆነች የ8ኛ ክፍል ተማሪ መኖራቸው ስጋታቸውን እጥፍ ድርብ ያደረገባቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
ቦንዳ ሸጠው የሚያገኙት ገቢ ስጋታቸውን መቅረፍ ስለማይችል ያለውን ነገር ተላምዶና ተቋቁሞ ከመኖር ውጭ ምንም አይነት አማራጭ አልነበራቸውም። ምርጫ በሌለው ሕይወት ውስጥ እየኖሩ ከቀኖች ሁሉ የተቀደሰች ቀን የተቀደሰ ዕድል አመጣችላቸው፤ የተቀደሰውን የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዕድልን፤ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ቤታቸውን ፈርሶ አዲስ በተሠራላቸው፤ ከነበሩበት ስቃይና ሰቀቀን ወጥተው በደስታ እንዲኖሩ የሕይወት ዕድል ሚዛን ፈቀደችላቸው።
ወይዘሮ አዳነች አብቼ ‹‹በክረምት ወቅት ዝናብ ሲጥል ልጆቼን የማስተኛበት ቦታ እያጣሁ አለቅስ ነበር፤ ወደ ቤት የሚገባው ጎርፍ ልጆቼን ይወስድብኛል እያልኩ አስባለሁ፤ ንፋስ በነፈሰ ቁጥር ጣራው ላይ የወደቀው የኤሌክትሪክ ገመድ እሳት ፈጥሮ አንድ ቀን ያቃጥለናል፤ በተለይም ወልዳ የተኛችውና የአዕምሮ ዘገምተኛ የሆነችው ልጅ ይጎዱብኛል ብዬ ከአቅም በላይ እፈራለሁ፤ እጨነቃለሁ። ቤቴን እንዳላድሰው የማገኘው ገቢ ከዕለት ጉርሳችን የሚተርፍ አልነበረም››ይላሉ።
ቤቱ ከማርጀቱ የተነሳ አንድ ቀን ወድቆ በእኔና በልጆቼ ላይ ጉዳት ማድረሱ አይቀርም ነበር ሲሉ ጊዜውን ለማስታወስ በሚመስል ትውስታ አጫውተውናል።
‹‹ለሰው ልጅ ትልቁ ሀብት ቤት ነው፤ ዛሬ አላህ ቆጥሮልኝ። የአዲስ ቤት ባለቤት ሆኛለሁ፤ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው፤ የቤት ባለቤት በማድረግ ከነበርኩበት ሰቀቀን ያወጣኝን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን፤ ባለሀብቶች በአጠቃላይ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳትፈው ቤቴን የሠሩልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ፤ ለእኔ እንደደረሱልኝ አቅም ለሌላቸው፤ ታመው ቤታቸው በላያቸው ላይ ለወደቀባቸው ይድረሱ›› ሲሉ እናታዊ ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።
ተማሪ አያት ዘይኑ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናት፤ የወይዘሮ አዳነች የአዕምሮ ዝግመት ያለባት ልጃቸው ናት። ተማሪ አያት ‹‹ዝናብ ሲጥል ቤታችን ያፈሳል፤ በፍሳሹ ምክንያት ትምህርቴን ለማጥናት እቸገር ነበር፤ ዛሬ ቤታችን ተሠርቶልናል፤ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ በትምህርቴ በርትቼ ዶክተር በመሆን ዜጎችን ያለምንምን ክፍያ አገለግላለሁ።›› የሚል ምኞቷን ገልጻልናለች።
ዛሬ ቤታችን ታድሶ ከመኖር የበለጠ በጎነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው አስተምሮኛል፤ የተደረገልን ርዳታ በጎነትን እያሰብኩ እንዳድግና ለወገኖች እንድደርስ ትልቅ ተነሳሽነት ፈጥሮብኛል ስትል ሐሴት በመላው ስሜት አውግታናለች።
በክረምት የበጎ ፍቃድ መርሐ ግብር አገልግሎት፤ የአቅመ ደካማዎችን ቤት በማደስና በመሥራት ኑሯቸውን የማሻሻል፤ የሰቆቃ ሕይወት እንባን የማበስ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ በበጎ ፍቃድ መርሐ ግብር እየተሠራ ያለውም ሥራ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
አቶ ይማም ሳይድ ሌላኛው፤ በኮልፌ ቀራንዮ በወረዳ ዘጠኝ በፍሳሽ ቤት የአለጧሪና የአለቀባሪ የሚኖሩ አቅም ደካማ ናቸው፤ አብሯቸው የሚኖር ልጅም ሆነ የሥጋ ዘመድ የላቸውም፤ እንደ አቅማቸው ያገኙትን ሥራ በመሥራት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሙላት የሚታትሩ አዛውንት ናቸው።
‹‹የምሠራው ሥራ ከዕለት ጉርስ የሚያልፍ አልነበረም፤ ከዕለት ጉርስ የሚተርፍ ባለመሆኑም በላዬ ላይ ዝናብ እየወረደብኝ ለመኖር ተገድጃለሁ፤ በብርድና በስቃይ ዓመታትን ኖሬያለሁ፤ ዝናብ ሲጥል ግቢው ጭቃ ስለሚሆን እየወደኩ ጉዳት ይደርስብኝ ነበር፤ በክረምት በጎ ፍቃድ ደጋግ ወገኖቼ ቤቴን ሠርተውልኛል፤ ከክረምት ሰቀቀን፤ ከበጋ ፀሐይ ወጥቻለሁ፤ ለካስ የሚያስበን ወገን አለን፤ በበጎነት ላደረጉልኝ እርዳታ ፈጣሪ አብዝቶ ይክፈላቸው›› ሲሉ ነግረውናል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ንቅናቄ ተፈጥሮ እየተሠራበት ያለው አቅመ ደካማዎችን ዝቅ ብሎ የማየት፤ የጎደላቸውን፤ የቸገራቸውን የመሙላት፤ ኑሯቸውን የማሻሻል ሥራ ይበል የሚያስብል ነው፤ ተጠናክሮ ይቀጥል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ቤቴ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከመሠራቱ በፊት እያፈሰሰ ለልጆቿቸውም ሆነ ለእሳቸወ አስቸጋሪ እንደነበር አቶ ታዲዮስ ሰመረ ነግረውናል።
‹‹ በመካኒክ ሙያዬ የማገኘው ገቢ ከእኔና ከቤተሰቦች የዕለት ጉርስና ከልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ የሚሻገር አይደለም፤ በዚህ ምክንያትም በክረምት ወቅት የሚያፈሰውን ቤቴን ማደስም ሆነ መሥራት አልቻልኩም። ያለኝ አማራጭ ዝናቡን ለማስቆም ሸራ ማልበስ፤ በቆርቆሮ በፕላስተር ጣራውን መጠገን ነው፤ እሱም ዘላቂ መፍትሔ አልነበረም፤ በሚያፈስና በእርጅና ሊወድቅ በአዘመመ ቤት መኖር ፈታኝ ነበር ›› ሲሉ አጫውተውናል።
የአዲስ አበባ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ትውልድ በትምህርት ከማፍራት ባለፈ ሰው ተኮር ሥራ እየሠራ ነው፤ እየሠራ ባለውም ሰው ተኮር ሥራ ቤቴን አፍርሶ በአዲስ መልኩ ሠርቶልኛል፤ ከነበርኩበት የሰቀቀን ኖሮ ወጥቼ የተሻለ ኑሮ እየኖርኩ ነው ሲሉ ደስታቸ ውን አጋርተውናል።
በወጣትነት ዘመናቸው ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ሀገርን አገልግለው ችግር ያጋጠማቸውን፤ ጤና ክዷቸው የአልጋ ቁራኛ ያደረጋቸውን ዜጎች እንባ ለማበስ እየተሠራ ያለው ሥራ የበጎነት ፍቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም