የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ የብረት ጎተራዎች ለአርሶ አደሩ እየተዳረሱ ነው

አዲስ አበባ፡የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ የብረት ጎተራዎችና የተሻሻሉ ከረጢቶች ለአርሶ አደሩ የማዳረስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

“ከረሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) የድህረ ምርት ብክነት መከላከልን አስመልክቶ ባቀረቡት ጥናት እንዳመላከቱት፤ በዓለም ደረጃ በየዓመቱ ከፍተኛ ምርት ይባክናል፡፡ በኢትዮጵያ አነስተኛ አርሶ አደሮች ደክመው ያመረቱትን ምርት በባሕላዊ መንገድ የሚያስቀምጡ በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ይባክናል፣ ይሰረቃል፤ በተለያዩ ነፍሳት ይጠፋል፡፡ የምርት ማከማቻ ዘዴዎች ኋላ ቀር በመሆናቸው በጥራትና በመጠን ብክነት ይከሰታል ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ የድህረ የምርት ብክነትን ለመከላከል ቀላል የሆኑ የብረት ጎተራዎችንና

ረሃብን ለማጥፋት ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን የድህረ ምርት ብክነትን መከላከል አስፈላጊ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መንግሥት እ.ኤ.አ ከ2023 ጀምሮ ሀገራዊ የድህረ ምርት አያያዥ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ሥራዎች እየሠራ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሮች ምርታቸውን የሚያከማቹት በጉድጓድ ውስጥ በመሆኑ ከአስር ኩንታል ምርት ውስጥ እስከ አራት ኩንታል ይበላሻል። መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ የጥራት ልዩነት ሳይኖር አከማችቶ ማስቀመጥ የሚያስችሉ ተሻሽለው የመጡ ከረጢቶችንና የብረት ጎተራዎችን በማቅረብ ላይ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

እንደ መለስ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በፖሊሲ፣ በአዋጆች፣ በመመሪያዎችና አጠቃላይ በማበረታቻ ሥራዎች ውስጥ በሚሠሩ ስትራቴጂዎች ውስጥ የድህረ ምርት ብክነት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው። ለአዝዕርት፤ ለአትክልትና ፍራፍሬ ሰብልና ለእንስሳት ተዋፅዖዎች ምን አይነት የምርት ማጓጓዣዎችና ማከማቻዎችን መጠቀም አለብን የሚለው ተለይቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፤ ደቡብ ኢትዮጵያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለአርሶ አደሩ የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው። በማኅበራት፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንቨስተሮች ዘመናዊ የምርት ማከማቻ እየተጠቀሙ ነው። በዚህም ውጤት ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።

በአዝዕርት ሰብል ከ20 እስከ 30 በመቶ የምርት ብክነት አለ ያሉት መለስ (ዶ/ር)፤ ይህንን እኤአ በ2030 ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። በአትክልትና በሰብል በፍራፍሬ ምርቶችን ላይ ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚሆን የምርት ብክነት አለ፤ ይህንን ብክነት በ2030 በግማሽ የመቀነስ እቅድ አለ። በአጠቃላይ እኤአ በ2050 የድህረ ምርት ብክነትን አምስት በመቶ በታች የማድረስ ሥራ ሀገራዊ እስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በዓመት ከ12 ሚሊዮን ቶን በላይ የድህረ ምርት ብክነት አለ ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፤ ብክነት የሚደርሰው ከምርት ስብሰባ ጀምሮ እስከ መጠቀም ባለው ሂደት ውስጥ ነው። በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚባክነው ምርት 46 ሚሊዮን ዜጋ መመገብ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በሀገር ደረጃ 22 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠላቸውም። ከስምንት እስከ 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ደግሞ የእለት ቀለብ እርዳታ ተሰፍሮ የሚሰጣቸው አሉ። ይህን ችግር ለመፍታትም ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን የምርት ብክነትን በመከላከል ረገድ እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል ።

የተሻሻሉ የምርት መያዥ ከረጢቶችን ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው፡፡ በዚህም በብዙ የሀገሪቷ ክፍሎች የምርት ብክነትና ብክለትን መጠበቅ እየተቻለ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአርሶ አደሩን ፍላጎትና አቅም መሠረት በማድረግ መንግሥት የተለያዩ ሥልጠናዎችንና ማበረታቻዎችን እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በሞገስ ፀጋዬ እና በአዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You