ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን ለማስመለስ

ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ማፍራት በአፍሪካና በተለያዩ ታዳጊ ሀገራት ትልቅ ሀገራዊ ችግር ሆኖ ቆይቷል። ቀደም ሲል ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ማፍራት ተጠያቂነትን ለማስከተል በተደረገው ጥረትም ከሕግና ፍትሕ አካላት በኩል ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሙሉ የሕግ ማሕቀፍ እንደሌለና መረጃዎችም የተጠናከሩ አለመሆናቸው ተገልጾ ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ መኖሩ ቢታወቅም ወንጀሉን ለመከላከል ምንጩ ያልታወቀ ንብረት መውረስን መሠረት ያደረገው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ከግለሰቦች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ጋር እንዲጣጣም አድርጋ እያዘጋጀች ይገኛል።

ምንጩ ያልታወቀ ንብረትንም ረቂቅ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት እስከ 10 ዓመት እንዲሁም 10 ሚሊዮን ብርና ከዛ በላይ ያሉትንም ጉዳዮች ተጠያቂ እንደሚያደርግ አዋጁ አስቀምጧል፡፡

ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምንጩ ከማይታወቅ ንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከፍትሕ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ለመሆኑ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ፋይዳው ምንድነው፤ አዋጁ ያሉበት ስጋቶችስ የሚሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማጣራት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዳነ መለሰ ፤ በሥራ ላይ ያለው የንብረት ማስመለስ አዋጅ ውስንና ወጥ አለመሆን፣ መንግሥት የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመከላከል ካለው ቁርጠኝነት እንዲሁም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ለአዋጁ መውጣት ምክንያት መሆናቸው ያነሳሉ፡፡

ረቂቅ አዋጁ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት የፍትሐብሔር ተጠያቂነት በሁሉም ሰውና በሕግ ሰውነት ባላቸው ተቋማት ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን ያስቀመጠ ነው ይላሉ፡፡

የአዋጁ መነሻ ሃሳብ ከተባበሩት መንግሥታት ፀረ ሙስና ኮንቬንሽን የመነጨ መሆኑንና ወቅታዊና አስፈላጊ በመሆኑ የሚደገፍ ነው ያሉት፡፡

የንብረት ማስተዳደርን በተመለከተ በአዋጁ የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊነት እንደሚወስድ አመላክተው፤ ይህም ግልጽነት የጎደለው አሠራር እንዳያስከትል እራሱን የቻለ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ቢቋቋም የተሻለ ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ ፡፡

በንብረት ማስመለስ ሂደት የሚገኘው ሀብት በአዋጁ እንደተቀመጠው ከሆነ በፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ ላይ ለተሠማሩ አካላት አቅም ግንባታ እንደሚውል ያመለክታል ያሉት አቶ አዳነ፤ ነገር ግን የፀረ ሙስና ትግል ብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያካትት በመሆኑ የሚገኘው ሀብት ለተለያዩ ተቋማት ለትውልድ ሥነምግባር ግንባታ ቢውል መልካም መሆኑን ይገልጻሉ ፡፡

በሌላ በኩል በሀብት ማስመለስ ሥራው ወንጀሉን የሚጠቁመው አካል ደኅንነት ለመጠበቅ እንዲያስችልም የመረጃ ማሰባሰብ ሥራው ዲጂታል መሆን አለበት፡፡ ይህም በአዋጁ በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ እንደሚሉት፤ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 25 ላይ በሚወረስ ንብረት ላይ ሦስተኛ ወገን መብት ካለ ማስረጃ አቅርቦ ማስቀየር ይችላል የሚል ሲሆን እዛው አንቀጽ ላይ ንዑስ ቁጥር አራት ላይ ግን በዋናው ገንዘብ ብቻ ይላል፡፡ ይህም በተለይም ባንኮች በንብረት የሚመሠረቱትን የመያዣ መብት የሚገድብና የወለድ ማስከፈል መብታቸውን የሚከለክል በመሆኑ መታየት ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል የሚወረሰው ንብረት ፋብሪካ አልያም ሌላ ንብረት ሊሆን ይችላል የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ይህም የሚተዳደርበት ሥርዓት እና የሚበላሹ ንብረቶች የሚወገዱበት ሥርዓት በአዋጁ በግልጽ ቢቀመጥ የተሻለ ይሆናል ይላሉ፡፡

አቶ ጌታቸው፤ የንብረት ግምት ማውጣት ለአዋጁ ተፈጻሚነት ፈታኝ የሚሆን ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ንብረት የሚገምት ተቋም ባለመኖሩ ገማች ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

በዋናነት አዋጁ የፋይናንስ ተቋማትን የብድር ሥርዓት ሊያዛባና ባንኮችም የሰጡት ብድር ተመላሽ እንዳይሆን ስለሚያደርግ በጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

ስለአዋጁ ዓላማ ማብራሪያ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትር ወይዘሮ ሐና አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ የሀብት ማስመለስ አዋጁ በሀገሪቱ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የኢኮኖሚ ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኙ ንብረቶችን ለማስመለስም ቁልፍ ሚና አለው ይላሉ።

ከዚህ ቀደም ያሉት ሕጎች ውስንና የተበታተኑ መሆናቸውን አንስተው፤ የሀብት ማስመለስን በሚመለከት ሁሉን አቀፍና አንድ ወጥ የሆነ ሕግ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

የኢኮኖሚ ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪና ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ረቂቅ አዋጁ ይህንን ለማስቀረት ድንበር ተሻጋሪ ሥራዎችን መሥራት የሚያችል ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በዚህ አዋጅ የፍትሐብሔር ተጠያቂነት በሁሉም ሰውና በሕግ ሰውነት ባላቸው ተቋማት ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን አንስተው፤ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን አዋጁ ከመውጣቱ በፊት እስከ 10 ዓመት ያሉ ጉዳዮችን ማየቱ የሀገሪቱን የመረጃ አያያዝ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ያብራራሉ፡፡

አዋጁ ወጥ የሆነ የንብረት ማስመለስ አስተዳደር ሥርዓት ሊዘረጋ የሚችልና በወንጀል የተገኘ ንብረትን የማስመለስ፣ ማጣራት፣ መያዝ፣ ማገድና መክሰስ የሚሉ በዝርዝር ጉዳዮችን የሚያስቀምጥ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You