‹‹ፍቅር ወጪ ቆጣቢ ነው›› ሲሉ ሰምቼ ነበር መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባዘጋጀው አንድ መድረክ ላይ:: ‹‹ፍቅር ካለ አንድ እንጀራ ለዘጠኝ ይበቃል›› የሚል ሀገርኛ ብሂልም አለ:: የቁጥሩ ብዛትና የምግቡ አይነት ምናልባት ከአካባቢ አካባቢ ይለያይ ይሆናል:: ብቻ ግን ፍቅር ካለ ትንሽ ነገር ያጠግባል::
‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› የሚባለው አባባል ገላጭ የሆነ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው:: አንድ ሰው እየተነጫነጨና እየተቆጣ ብዙ ወይም የቅንጦት የሚባል ውድ ምግብ ከሚሰጠን፤ በፍቅር ቁራሽ ዳቦ ቢሰጠን ታስደስተናለች:: ያቺ ቁራሽ ዳቦ የሕሊና ጥጋብ ታጠግበናለች:: የሰው ልጅ ልባዊ (አሳቢ) ነውና ከሥጋ ጥጋብ ይልቅ የሕሊና ጥጋብ ይበልጥበታል:: በሕሊናው የሚቀረጽ ነገር በመላ ሰውነቱ ላይ ሚና ይኖረዋል::
ለምሳሌ፤ ሰዎች ከባድ ኅዘን ላይ ሲሆኑ ምግብ አይበሉም:: ለምን? ሕሊና ላይ የተፈጠረው የመረበሽ ነገር ሥጋዊ የሆነውን የምግብ ፍላጎት የመቆጣጠር አቅም አለው ማለት ነው:: የትዝብታችን ጭብጥ ስለምግብ ለማውራት አይደለም:: ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ›› የሚለው ሀገርኛ ብሂል ከሕሊና እና ከቅንነት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሰብ ነው::
የዛሬ ትዝብታችን ቅንነቶቻችንን መታዘብ ነው:: በብዙ ቦታዎች የምናስተውለው ችግር ነው:: ምንም እንኳን ሁላችንም የምናስተውለው ቢሆንም በየአጋጣሚው ትዝ የሚሉኝና የሚገርሙኝን ከዓመታት በፊት ያጋጠሙኝ ሁለት ገጠመኞች መነሻ ላድርግ::
አዋሽ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ ውስጥ ነው:: ደንበኞች በተቀበልነው የወረፋ መጠበቂያ ትኬት ቁጥር መሠረት ወረፋችንን እየጠበቅን ነው:: አንድ ደንበኛ፤ ገባና ቅጽ ከሞላ በኋላ ሠራተኛ የሌለበት ባዶ መስኮት ላይ ቆመ:: ከባዶው መስኮት ቀጥሎ ያለው የባንኩ ሠራተኛ (ቴለር) ሰውየውን አናገረው፡ ሰውየውም ወደ ቴለሩ ሄደና የሞላውን ቅጽ ዘረጋ:: የባንክ ቴለሩ ቅጹን ሳይቀበል ሰውየው ወረፋ መያዝ እንዳለበት ነገረው:: ሰውየው (ደንበኛው) ‹‹ታዲያ ለምን ጠራኸኝ?›› ሲል ደነፋ:: ቴለሩም ደንበኛው የቆመበት መስኮት ለጊዜው ሠራተኛ እንደሌለውና እዚያ መቆሙ ምንም ጥቅም እንደሌለው ነገረው:: ደንበኛው ሊሰማ ነው እንዴ!
ከብዙ ልመና እና ማግባባት በኋላ የባንኩ ሠራተኛ ወጣት ነበርና ትዕግሥቱ አለቀ፤ ወደ መሰዳደብና መዘላለፍ ገቡ:: ሁነቱን ሲታዘቡ የነበሩ ሰዎች ጣልቃ ገብተው ሰውየውን (ደንበኛውን) ፈረዱበት:: ቴለሩንም አመስግነው ‹‹አንተ ዝም ብትል ይሻላል›› ብለው ለምነው ዝም አለ:: ሰውየውም የሞላውን ቅጽ እየቀደደና እየተሳደበ ጉዳዩን ሳይፈጽም ሄደ::
ምንም እንኳን ሰዎችን በአለባበስና በአካላዊ ገጽታ ምንነታቸውን ማረጋገጥ ባይቻልም፤ ያ ሲያተራምስ የነበረ ሰውዬ የተማረ የሚባል አይነት አለባበስና አካላዊ ገጽታ ያለው ነው:: ውድ ቦርሳ ያነገተ ነው:: የሥልጡንነት አርዓያ መሆን የሚገባው ነበር::
እዚህ ላይ አንድ ነገር ሊባል ይችላል:: ከሥራ ሥነ ምግባር አንፃር ቴለሩ ታጋሽ መሆን አለበት፤ ግን በታገሰው ቁጥር ሰውየው ጭራሽ እየባሰበት ሄደ:: ስለዚህ ሰውየውን ላለማስከፋት ቴለሩ ምን ማድረግ ነበረበት? ያለወረፋው ማስተናገድ? ይሄ ደግሞ ሌላ የመርሕ ጥሰት ነው::
አንዳንድ እንዲህ አይነት ሰዎች አሉ:: ትሕትና እና ቅንነት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሲደረግላቸውም የማይወዱ፤ በትሕትና እና በቅንነት ባናገሯቸው ቁጥር ጭራሽ የሚብስባቸው አሉ:: ‹‹ሞኝ ሲያከብሩት የፈሩት ይመስለዋል›› የሚባለው አይነት ማለት ነው::
የዚህን ተመሳሳይ አንድ ልጨምር:: የመንግሥት ሠራተኞች ማመላለሻ የሆነው ‹‹ፐብሊክ ሰርቪስ›› ውስጥ ያጋጠመኝ ነው:: ሰርቪሱ ለመጫን እና ለማውረድ ሲቆም፤ እንደ በቆሎ እና ቆሎ ያሉ ነገሮችን ይዘው በበር እና በመስኮት በኩል ብቅ የሚሉ ልጆች አሉ:: አሽከርካሪው ማንም የሰርቪሱ ተጠቃሚ እንዲህ አይነት ነገሮችን እንዳይገዛ አስጠንቅቋል መሰለኝ:: እኔም በዚያ ሰርቪስ የሄድኩት የዚያን ቀን ነው::
ላምበረት መናኸሪያ ፊት ለፊት ካለው ፌርማታ እንደቆመ፤ በቆሎ የያዘች ልጅ ወደ ሰርቪሱ በር መጣች:: አንደኛው ተጠቃሚ ሊገዛ ሲል አሽከርካሪው ጮኸበት:: ‹‹ይቅርታ!›› ብሎ ተወው:: አሽከርካሪው ‹‹እንዳትገዙ ብዬ አላስጠነቀቅኩም ነበር ወይ?›› ብሎ በቁጣ ጠየቀ:: ተጠቃሚውም ከዚህ በፊት በዚህኛው ሰርቪስ ሄዶ እንደማያውቅና ማስጠንቀቂያውን እንደማያውቅ በትሕትና ተናገረ:: ሌሎች የሰርቪሱ ቋሚ ተጠቃሚዎች ‹‹ገና ዛሬ ነው የመጣ›› እያሉ ለማግባባት ሞከሩ:: የፐብሊክ ሰርቪስ ተጠቃሚ በአንድ መስመር የሆነ ሁሉ ባገኘው ይሄዳል እንጂ የግድ በአንድ ተሽከርካሪ ብቻ አይሆንም::
አሽከርካሪው አሁንም አምርሮ ይቆጣል:: ያ እንግዳ ተጠቃሚ ሰውየም ያለመታከለት ‹‹ይቅርታ!›› ይላል:: የአሽከርካሪው ቁጣ ግን እየባሰበት ሄደ:: ይህኔ ተጠቃሚውም ከብዙ ይቅርታ በኋላ ‹‹እንዴ! አልገዛሁም እኮ! ‹አይቻልም!› አልከኝ ተውኩት! ለማሰቤም ይቅርታ ጠየቅኩህ!›› እያለ ፈርጠም ብሎ ተናገረ:: ይህኔ አሽከርካሪው ቁጣው ጨምሮ ‹‹ውረድ!›› አለው:: ተጠቃሚውም እልህ ውስጥ ገባና ‹‹አልወርድም!›› አለ:: አሽከርካሪው ዳር አስይዞ ቀበቶውን ፈተና በሩን በርግዶ ወረደ:: የተጠቃሚዎች መውጫ በር ግን እንደተዘጋ ነው:: ተጠቃሚው ከቦታው ተነስቶ ወደ በሩ ሲንደረደር ከፊት ያሉ ሰዎች ያዙት:: መስኮት ከፍቶ አሽከርካሪውን ‹‹ወንድ ከሆንክ ክፈተው!›› እያለ መሳደብ ጀመረ:: አሽከርካሪው ወደ ቦታው ተመልሶ በስሜት ረስቶት የነበረውን በር ከፈተና ሰውየው ካልወረደ እንደማይሄድ ተናገረ::
ከብዙ ትርምስ፣ ጭቅጭቅና ልመና በኋላ ታርቀው ጉዞ ተጀመረ::
እነዚህን ሁለት ነጠላ ምሳሌዎች ያመጣሁት ለማሳያ እንጂ ሁሉንም ይወክላሉ ብዬ አይደለም:: እንዲህ አይነት ብዙ አጋጣሚዎች አሉ:: ግን ለማሳያ እና ለምሳሌ ይሆናሉ::
እስኪ ልብ በሉ! በመጀመሪያ ሰርቪሱ ውስጥ የገባው ተጠቃሚ ማስጠንቀቂያውን አያውቅም:: ግዴለም! የሰርቪስ ሕግና ደንብ ስለሆነ (ለበቆሎና ለቆሎ ልዩ ዝርዝር ባይኖረውም) ተጠቃሚ እስከሆነ ድረስ ክልክል መሆኑን ማወቅ ነበረበት እንበል:: በሁለተኛ ደረጃ ግን አልገዛም፤ ‹‹ተው!›› ሲባል ትቶታል:: በዚያ ላይ ደጋግሞ ይቅርታ ጠይቋል:: ሰው እንዴት ይቅርታ በተጠየቀ ቁጥር እየባሰበት ይሄዳል?
ከአንዳንድ ሰዎች የተረዳሁት ነገር ከትሕትና፣ ከቅንነት እና ከይቅርታ ይልቅ ግልምጫ፣ ስድብ እና ቁጣ ይገዛቸዋል:: ለምሳሌ የታክሲ ረዳቶችን ልብ በሉ! ተጠቃሚዎች በቁጣ ‹‹ወራጅ አለ!›› ሲሉ፤ ለምን በቁጣ ይናገራሉ እያልኩ እናደድ ነበር:: የሚገርመው ግን ረዳቶቹ ተሽቁጥቁጠው የሚያስተናግዱት የሚያመናጭቃቸውን ሰው ነው:: ስለትሕትና እና ቅንነት ታክሲውን ጥቅስ በጥቅስ ቢያደርጉትም በቅንነት የሚያናግራቸውን ሰው ግን ያመናጭቃሉ:: መልስ እንኳን በትሕትና ሲጠየቁ ‹‹ይሰጥሃላ! ልትሞት ነው እንዴ!›› እያሉ ይናገራሉ:: በትሕትና ‹‹እዚህ ጋ ታወርደኝ›› ሲባሉ ‹‹አደባባዩ ላይ አይሻልሽም?›› እያሉ ያሾፋሉ:: እንዲህ አይነት ሰዎች ከትሕትና ይልቅ ግልምጫ ይገዛቸዋል ማለት ነው::
ትሕትና እና ቅንነት የመሠልጠን ምልክት ነው:: በተቃራኒው ስድብ እና ግልምጫ የኋላቀርነት እና የበታችነት ስሜት ምልክት ነው:: መሳደብን እንደ ድፍረት የሚያዩ ይኖሩ ይሆናል፤ ግን አይደለም፤ የተጠራጣሪነት እና በራስ ያለመተማመን ምልክት ነው:: በራሱ የሚተማመን ሰው ቅን እና ትሑት ነው::
ቅንነት ጤና ነው:: በቅንነት ስናስብ የሰውነታችንን ህዋሶች አንጎዳም:: ህሊናችንን አንረብሽም:: የጥፋተኝነት ስሜት አይፈጠርብንም:: በውስጣችን የፀፀት አሻራ አይቀመጥብንም:: እልህ ግን በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በሳይንስም የተወገዘ ነው:: ለጤና ጎጂ ነው:: የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት በቀል እና እልህ ውስጥ ስንገባ የጭንቅላታችን ህዋሶች ይጎዳሉ::
ቅንነት ማኅበራዊ ሕይወትን ለማሳለጥ ብቻ ሳይሆን ለአካላዊና አዕምሯዊ ጤናም ነውና ቅን እንሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም