ሀገራችን ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል እያደረገች ያለችው ጥረት እና እየተመዘገበ ያለው ስኬት እንደ ሀገር የትናንት የረሃብ ታሪካችንን የሚቀይር፤ ከራሳችን አልፈን ለሌሎች መትረፍ የሚያስችለንን አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ትልቅ ሀገራዊ መነቃቃት ነው። ይህም ለብዙ ሀገሮች በማሳያነት የሚጠቀስ፣ ተጨባጭ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ መሆንም ችሏል።
ሀገሪቱ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊ መሬት፣ ተስማሚ አየርና ውሃ እንዲሁም የሰው ሀብት ባለቤት ብትሆንም፣ እነዚህን አቅሞች አቀናጅቶ ወደ ልማት መለወጥ የሚያስችል ፖሊሲና የመንግሥት ቁርጠኝነት ሳይኖር በመቆየቱና አስተማማኝ ሠላም ማስፈን ባለመቻሉ ለምግብ እህል እጥረት፤ ከዚያም ባለፈ ለረሃብ አደጋዎች የተጋለጥንባቸው ወቅቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው በየአስር ዓመቱ በቀጣናው የሚከሰተው ድርቅ፤ የምግብ እህል እጥረት ችግራችንን በማባባስ፤ ለብዙ ዜጎቻችን ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ለሆኑ የረሃብ አደጋዎች ተጋላጭ ሲያደርገን ቆይቷል። ይህ ሁኔታ ያደረሰብን ጉዳት እንዳለ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብሔራዊ ክብራችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎ መኖሩም ይታወቃል።
ይህንን ሀገራዊ ችግር ለዘለቄታው ለመሻገር ከለውጡ መንግሥት ጀምሮ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ከፍ ባለ መነቃቃት እና ቁጭት ወደ ሥራ ገብተናል። ይህን ተከትሎም የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ዘላቂነት ያላቸው ተከታታይ ሥራዎች እያከናወንን ተጨባጭ ስኬቶችንም እያስመዘገብን እንገኛለን።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ሀብታችን የተሠማራበትን ይህንን ዘርፍ ምርታማ ለማድረግ የተጀመሩ ሀገራዊ ጥረቶች ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ፤ በየወቅቱ እየፈተነን ያለውን የረሃብ አደጋ ለዘለቄታው በመሻገር በምግብ እህል ራሳችንን እንድንችል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል፤ ያለንን አቅም ተጠቅመን በዓለም አቀፍ ገበያ ተፎካካሪ እንድንሆን የሚያደርገንም ጭምር ይሆናል።
በግብርናው ዘርፍ ያለንን ሀገራዊ አቅም በሚገባ አውቆ መጠቀምን መሠረት ያደረገው የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ፤ የዘርፉን ምርታማነት በጥራት፣ በብዛት እና በዓይነት ማሳደግን፤ ከሁሉም በላይ በምግብ እህል ራሳችንን እንድንችል፤ ከዚያም ባለፈ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሚያስችል ራዕይ ያነገበም ነው።
እስካሁን በተከናወነው ተግባርም በበጋ የመስኖ የስንዴ ልማት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፤ በዚህም በየዓመቱ ሰኬታማ መሆን እየተቻለ ነው፡፡ የመስኖ ልማቱ በሀገሪቱ የሚመረተውን የስንዴ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገው ይገኛል፡፡ አጠቃላይ የስንዴ ልማቱ ከውጪ ይገባ የነበረውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ዶላር ማዳን አስችሏል። ምርቱን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እያስቻለም ነው፡፡
በሌማት ትሩፋትም ሆነ በአረንጓዴ ዐሻራ፤ እንደ ሀገር በምግብ እህል ራስን ከመቻል ባለፈ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ለማስቻል እየተደረገ ያለው ሀገራዊ ጥረትም፤ አሁን ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። ይህም ከትናንት የጠባቂነት የታሪክ ምዕራፍ ወጥተን ሙሉ በሙሉ በራሳችን መቆም እንደምንችል በሚገባ አመላክቷል።
የእርሻ መሬት በማስፋት ብቻ ሳይወሰን የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገው የመንግሥት የለውጥ አቅጣጫ፤ በተለይም ሀገር እንደ ሀገር ከምግብ እህል ጠባቂነት ለዘለቄታው እንድትወጣ በማድረግ እንዲሁም ትርፍ በማምረት ከረሃብ እና ከረሃብ ነፃ የሆነች ሀገርን እው ን ማድረግ ታሳቢ ያ ደረገ ነው።
ይህም በብሔራዊ ክብራችን ላይ መጥፎ ጥላ አሳርፎ የኖረውን የረሃብተኝነት ታሪክ በመለወጥ፤ ብሔራዊ ክብራችንን ሙሉ በማድረግ፤ አንገታችንን ቀና አድርገን መጓዝ የሚያስችለን አዲስ የታሪክ ትርክት ለመፍጠር በብዙ ቁጭት የጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሀገራዊ መነቃቃት አካል ነው።
“ከረሃብ ነፃ የሆነች ዓለም” በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ እያስተናግድን ያለነው፣ ከረሀብ ነፃ የሆነች ሀገር ለመፍጠር እያደረግነው ያለው ጥረት ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ባለበት ሁኔታ በመሆኑ፤ ለእኛ ለኢትዮጵያውን ትልቅ ትርጉም ይሰጠናል፤ ለጥረታችን ስኬት አበረታች የሞራል ስንቅ ይሆነናል።
ከረሃብ ነፃ የሆነች ዓለም ለመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ይህ መነሳሳት፤ ዓለማችን ያላትን አቅም በኃላፊነት መንፈስ በጋራ ማልማት ከተቻለ፤ ያለብዙ ውጣ ውረድ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፤ ይህም ለብዙዎች እፎይታ የሚፈጥር፤ ለመጪዎቹ ዘመናት ተስፋም ይሆናል!
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም