አገልግሎቱ በሩብ ዓመት ከ11 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ

  • ከ90 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ፦ በ2017 በጀት ሩብ ዓመት ከ11 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። ከ90 ሺህ 570 በላይ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረጉንና ለሦስት ሺህ 376 ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተጠቁሟል።

የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ትናንትና በሰጡት መግለጫ በሩብ ዓመቱ ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከአዲስ ደንበኞች አገልግሎቶች፣ ከማያገለግሉ ንብረቶች ሽያጭ እና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች 11 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 11 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

የገቢ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንጻር 97 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፤ ከአጠቃላይ ገቢው አንጻር ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብሩ የተገኘው ከኢነርጂ ሽያጩ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪ በሩብ ዓመቱ 120 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 90 ሺህ 573 አዳዲስ ደንበኞች ተጠቃሚ በማድረግ የዕቅዱን 75 በመቶ ማሳካት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

አጠቃላይ የተቋሙን የደንበኛ ቁጥር ወደ አራት ሚሊዮን 850 ሺህ 800 ማሳደግ እንደተቻለ አቶ መላኩ አስታውቀዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት ሰፊ የቅድመ መከላከል ጥገና፣ የአስቸኳይ ጥገና፣ የማሻሻያና መልሶ ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ አዲስ 31 የገጠር ቀበሌዎችን ከዋናው ግሪድ በማገናኘት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 26 የገጠር ቀበሌዎችን በማገናኘት 83 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

የኃይል መቆራረጡን በሚፈለገው ልክ መቀነስ አለመቻሉ፣ የቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ ወይም ምላሽ አሰጣጡ ተገልጋዮች በሚጠብቁት ልክ አለመሻሻሉና ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቃቸው በሩብ ዓመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ያሉት አቶ መላኩ፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተሠሩ የተለያዩ ሥራዎች ለ3 ሺህ 376 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ተናግረዋል።

በሩብ ዓመቱ የተለያዩ የክፍያ አማራጮችን በማስፋፋት በተለይ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።

አቶ መላኩ እንደገለጹት፤ የኢነርጂ ታሪፍ ማሻሻያውን በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተው፤ የታሪፍ ማሻሻያው በየአራት ዓመቱ ተግባራዊ የሚደረግ ሆኖ ሳለ ላለፉት ሁለት ዓመታት ማሻሻያ አልተደረገም።

ከመስከረም አንድ ቀን 2017 ዓ.ም የጀመረው የታሪፍ ማሻሻያም ጊዜውን ያማከለ፣ ተመጣጣኝ እና የተሻለ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽንና የብልሽት ማስተካከያ ቆይታ ጊዜን የማሳጠር ሥራ መሻሻሉን ተናግረው፤ ይህንንም ይበልጥ ለመቀነስ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽሉ በርካታ ፕሮጀክቶችና የእድሳት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሩብ ዓመቱ በተጣሩ የብልሹ አሠራር ጥቆማዎች መሠረት 20 የአገልግሎቱ ሠራተኞችን ተጠያቂ መደረጋቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

 

Recommended For You